Fana: At a Speed of Life!

ከሕመም ጋር አራት ልጆችን ያለአባት የማሳደግ የእናትነት ብርቱ ፈተና…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጸሃይ ተሻለ ትባላለች፤የአዲስ አበባ ነዋሪ ስትሆን ሕመምተኛ እና የአራት ልጆች እናት ናት፡፡

የሕይወት መልኩ ብዙ ነው፣ አንዴ ጥሩ የሆነው ሌላ ጊዜ መጥፎ ገጽታውን ሊያሳይ ይችላል፡፡

ጸሃይ ተሻለም ከባለቤቷ ጋር ትዳር ስትመሰርት ደስተኛ ነበረች፤ ትዳራቸው የሰመረ ሆኖም ጥንዶቹ በልጅ ተባረኩ፡፡ ልጅ ሲመጣ ትዳር ይደምቃልና የጸሃይና ባለቤቷ ፍቅርም በልጆች ፍቅር ታጅቦ ዓመታትን አሳለፈ፡፡

ይሁን እንጂ ጸሃይና ባለቤቷ ሶስት ልጆችን ከወለዱ በኃላ በተለያዩ  ምክንቶች ትዳራቸው እክል አጋጠመው፤ ጥንዶቹ ልዩነትን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ወደ ግጭት አካላዊ ጉዳት አመሩ፣ በዚህ ውኔታ ላይም ጸሃይ አራተኛ ልጇን ነፍሰ ጡር እያለች ባለቤቷ ልጆቹን አደራ እንኳን ሳይል ጥሏት ጠፋ፡፡

ጸሃይ ከባለቤቷ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በመለያየታቸውም አሁን ላይ አራት ልጆችን ብቻዋን የማሳደግ ሃላፊነት  ተሸክማለች፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ከባለቤቷ ጋር ልጆችን ለማሳደግ እና ሕይወትን ለማሸነፍና በርካታ ውጣ ውረድ እንዳሳለፈች ትናገራለች፡፡

ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ.. በአሁኑ ወቅትም አባት የት እንዳለ ባለመታወቁ ከማይድን ሕመም ጋር አራት ልጆችን ለማሳደግ ብርቱ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ አንስታለች፡፡

ልጆቹን ለማሳደግና ትምህርት ለማስተማር ልብስ ከማጠብ ጀምሮ የተለያዩ አድካሚ ሥራዎችን እንደምትሰራ ነው የገለጸችው፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ባለው ሁኔታ መሰል ሥራዎችን በህመም እየተሰቃየች ሰርታ አራት ልጆችን ማሳደግ ከአቅሟ በላይ መሆኑን ለፋና ዲጂታል አስረድታለች።

ይህን ተከትሎም ልጆቿ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እና የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ጎዳና በመውጣት ለልመና መዳረጓን አብራርታለች፡፡

”ያን ቀን እንደወትሮው ቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ የለም፤ልጆቼን እያለቀስኩ አየኋቸው፤ ፊታቸው ጠውልጓል፤ እርቧቸዋልም፤ ከዛም የልጆቼን ርሃብ ለማስታገስ እግሬ ወደ አመራኝ ጎዳና ወጣሁ” ትላለች ልመና የወጣችበትን ቅጽበት ስታስታውስ።

በእርግጥ ጎዳና ወጥቶ እንደመለመን ከባድ ፈተና የለም የምትለው ጸሃይ÷ አማራጮቿን ሁሉ ሞክራ የልጆቿን ቀጣይ ሕይወት አደጋ ላይ ላለመጣል የቀራት ብቸኛ አማራጭ የሰዎችን ትብብር መጠየቅ እንደሆነ ተናግራለች፡፡

7ኛ ክፍል የሆነው የመጀመሪያ ልጇ እንደ እርሷ የማይድን ሕመም ተጠቂ መሆኑን ስትናገር እንባዋ ይተናነቃታል፡፡

ሁለተኛ ልጇ 2ኛ ክፍል፣ ሶስተኛ ልጇ የቅድመ መደበኛ ተማሪ እንዲሁም የመጨረሻ ልጇ ደግሞ የ1 ዓመት ከሶሶት ወር ዕድሜ እንዳላት ገልጻለች፡፡

እናትነት፣ አቅም ማጣት እና የልጅን ቀጣይ እጣ ፈንታ የመወሰን ከባድ ፈተና ከሕመሟ ጋር ተዳምረው በንግግሯ መሃል የምትለው ይጠፋታል፡፡

ከሁሉም በላይ ልጆቼን አስተምሬ ጥሩ ደረጃ እንዲደርሱ ፍላጎት አለኝ የምትለው ምስኪኗ እናት፤ ልጆችም በጥሩ ሁኔታ ትምህርታቸውን ተከታትለው የተቸገሩ ሰዎችን የመርዳት ሕልም እንዳላቸው እንደሚነግሯት አንስታለች፡፡

አሁን ላይ ከልጆቿ ጋር የምትኖርበት ቤት ለአደጋ የሚያጋልጥ ከመሆኑ በላይ ውሃ እና መብራት እንደሌለው እና ምቹ አለመሆኑን አብራርታለች፡፡

ልጆችን ተከታትሎ ማስተማርና የእለት ጉርስ መፈለግም የእናትነት የእለት ጭንቀቷ መሆኑን በተሰበረ ልብ ታስረዳለች፡፡

ስለሆነም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያለባትን ጽኑ ችግር ተረድተው እጃቸውን እንዲዘረጉላት እናት ጸሃይ ተማጽናለች፡፡

ባለታሪኳን ማግኘትና መርዳት ለሚፈልግ👉ጸሃይ ተሻለ ዘሪሁን፤ስልክ፣ 0923149392

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.