Fana: At a Speed of Life!

በየቀኑ ለ365 ቀናት ከማራቶን በላይ ርቀት የሮጠችው ብርቱ ሴት

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓመቱን ሙሉ በየቀኑ ከማራቶን በላይ ርቀት ሮጣ በብቃት ያጠናቀቀችው ብርቱ ቤልጄማዊት ሂልዴ ዶሶኜ ዕድሜዋ 55 ነው፡፡

በኬሚካል ኢንዱስትሪ ውስጥም የባዮ-ኢንጂነር ባለሙያ ሆና ታገለግላለች፡፡

በፈረንጆቹ 2024 የመጨረሻ ዕለት የመጨረሻ ሩጫዋን ስታጠናቅቅም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች አድናቆት በተሞላበት ጭብጨባ ተቀብሏታል፡፡

ከሥራዋ ጎን ለጎን 15 ሺህ 444 ኪሎ ሜትር ሮጣለች፤ በየቀኑም 42 ነጥብ 500 ኪሎ ሜትር ስትሮጥ ቆይታለች፡፡

የሩጫ መርሐ-ግብሯ መቋጨቱን ተከትሎም በመጠናቀቁ መደሰቷን ገልጻ፤ ከአካላዊ ድካሙ ይልቅ አእምሯዊ ጫናው እንደፈተናት ታነሳለች፡፡

እስከ አሁን በርካታ ቀናትን በተከታታይ የሮጠቸው አውስትራሊያዊቷ ኤርቻና ሙራይ ስትሆን÷ ለ150 ተከታታይ ቀናት በመሮጥ ዓለም ክብረ ወሰንን ይዛ መቆየቷ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ዶሶኜ በሴቶች የመጀመሪያዋ 365 ቀናት በተከታታይ ማራቶን የሮጠች ሴት ሆናለች።

በወንዶች ብራዚላዊው ሁጎ ፋሪያስ በፈረንጆቹ 2023 ለ366 ቀናት በተከታታይ ማራቶን በመሮጥ ባለክብረ ወሰን ነው።

ዶሶኜ በምትሮጥበት ወቅት መውደቅ፣ የሰውነት መላላጥ፣ ስብራት እና ሌሎች ችግሮች ገጥመዋት እንደነበር ትገልጻለች፡፡

ከዕለታት በአንዱ ቀን በሩጫ ላይ 27ኛ ኪሎ ሜትር ላይ ስትደርስ ወድቃ በጣቷ ላይ ጉዳት መድረሱን ታስታውሳለች፡፡

በዚህም ወደ ሐኪም ቤት ተወስዳ ከታከመች በኋላ ሩጫዋን እንደገና ከዜሮ ጀምራ በመጨረስ አድናቂዎቿን አጃኢብ አሰኝታለች፡፡

ማራቶኑን እና ሥራዋን እንዴት አጣጥማ እንዳስኬደች ስትናገር÷ “ሩጫዬ ከሥራዬ ጋር እንዳይጋጭ በጠዋት ገብቼ ሥራዬን በመጨረስ ከሠዓት በኋላ ሮጣለሁ” ማለቷን አልጄዚራ ዘግቧል።

የማራቶን ሩጫዋን እያካሄደች ለካንሰር ምርምር የሚውል 62 ሺህ ዶላር ገንዘብ ለማሰባሰብ የቻለች ጠንካራ ሴትም ናት፡፡

ዓመቱን ሙሉ የሮጠችውን ማራቶን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ እንደምታስመዘግብም ይጠበቃል፡፡

የሩጫዋን ውጤት በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ለማስመዝገብም የጂፒኤስ፣ የፎቶና የቪዲዮ እንዲሁም ገለልተኛ ምስክሮችን በማስረጃነት አሰናድታ ማመልከት ይጠበቅባታል።

ፕሮፌሽናል አትሌቶች ከውድድር በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ የማገገሚያ እረፍትና ክትትል በሚያደርጉበት ዘመን÷ የማጣሪያ ውድድር የሌለው ማራቶንን ያህል ፈታኝ ስፖርት በየቀኑ ለ365 ቀናት ሮጣ በስኬት ማጠናቀቋ ይገርማል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.