ሠራዊቱ ከተልዕኮው ባሻገር ሰፋፊ የልማት ሥራ እያከናወነ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ተልዕኮውን ከመፈፀም ጎን ለጎን ሰፋፊ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በመከላከያ ተቋማት የኮሪደር ልማት አካል የሆኑ የመሠረተ-ልማት ግንባታ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ግቢ እና በሎጂስቲክስ ማዕከሎች÷ እየተሠሩ ያሉ የግንባታ ሥራዎች፣ ማዕከሎችን ውብና ፅዱ የሥራ አካባቢ ለማድረግ እተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት አካል የሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ተመልክተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም መከላከያ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከተሰጠው ተልዕኮው ጎን ለጎን በዘርፈ-ብዙ እና የመሠረተ-ልማት ግንባታዎች እና የልማት ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎች አካል የሆነው የመሠረተ-ልማት ግንባታ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩም አሳስበዋል፡፡