Fana: At a Speed of Life!

የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የፓውዛና ስክሪን ገጠማ በቅርቡ እንደሚከናወን ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በቅርቡ የምሽት ጨዋታዎች ለማካሄድ የሚያስችሉ የውዛ መብራት፣ የጃይንት ስክሪን፣ የክብር እንግዶች የሚቀመጡበት ወንበር ገጠማ እንደሚከናወንለት ተገለጸ፡፡

አጠቃላይ የስታዲየሙ ግንባታ አፈጻጸም 82 ነጥብ 47 በመቶ መድረሱን የአማራ ክልል የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ ከፋና ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ አረጋግጠዋል፡፡

የስታዲየሙ ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ግንባታው የሚጠናቀቅበት ጊዜ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም በውጭ ሀገር በሚከናወን የዕቃ ግዥ መዘግየት ምክንያት በተባለው ጊዜ ሳይጠናቀቅ መቅረቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ የቀሩ ሥራዎች የምሽት ጨዋታዎች ለማካሄድ የሚያስችሉ የውዛ መብራት፣ የጃይንት ስክሪን፣ የክብር እንግዶች የሚቀመጡባቸው ወንበሮች ገጠማ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ቁሶች በመጓጓዝ ላይ በመሆናቸው በቅርቡ የገጠማ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሩ ትኩረት ከፍተኛ መሆን፣ የተለያዩ የግል እና የመንግስት አካላት የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ያላቸው ቁርጠኝነት በመልካም አጋጣሚ እንደሚነሱ ጠቅሰዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.