በኒው ኦርሊያንስ ህዝብ ወደተሰበሰበት መኪና የነዳው ግለሰብ የ10 ሰዎች ህይወት ቀጠፈ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ ኒው ኦርሊያንስ ህዝብ ወደተሰበሰበት መኪና የነዳው ግለሰብ የ10 ሰዎች ህይወት ቀጠፈ።
በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች በተጨማሪ 30 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ተሰምቷል።
በኒው ኦርሊያንስ ቦርቦን ጎዳና ላይ የተከሰተው አደጋው አሽከርካሪው ጉዳት ለማድረስ በማሰብና መስመሩን ጥሶ ሰዎች በብዛት ወደተሰበሰቡበት አካባቢ በመፍጥነት መንዳቱን ተከትሎ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
አሽከርካሪው አዲስ ዓመት በሚያከብሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ከመኪናው በመውጣት ተሸከርካሪው እንዲቃጠል ማድረጉም ነው የተገለፀው፡፡
በማህበራዊ ትስስር ገፆች በተለቀቁ ተንቀሳሽ ምስሎችም ሆን ተብሎ በተፈፀመው የትራፊክ አደጋ በቦርቦን ጎዳና ህይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች አስከሬን ታይቷል፡፡
የኒው ኦርሊያንስ ከተማ የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ቡድን÷ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት በማስከተሉ ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስታውቋል፡፡
በአካባቢው የነፍስ አድን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑም በቡድኑ ተገልጿል።
በከተማዋ የአዲስ ዓመት በዓልን ተከትሎ በሀገር ውስጥ እና ውጭ ጎብኝዎች ተጨናንቃ የነበረ ሲሆን ፖሊስ ሰዎች በአካባቢው ብዙ ሰዓት እንዳይቆዩ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር መባሉን ስካይ ኒውስ እና ፍሪ ፕሬስ ጆርናል ዘግበዋል፡፡