Fana: At a Speed of Life!

በመርካቶና አንዳንድ አካባቢዎች የደረሠኝ ቁጥጥሩ ውጤት አምጥቷል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መርካቶን ጨምሮ በሥምንት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ዋና ዋና የግብይት ሥፍራዎች ደረሠኝ በመቁረጥ እና ተያያዥ ጉዳይ ላይ እየተከናወነ ያለው ቁጥጥር ውጤት አምጥቷል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

ከተማዋ ማግኘት ያለባትን ገቢ በአግባቡ እንድታገኝ ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትን ማስፈን ትኩረት ተሰጥቶት የቁጥጥር እና ክትትል ሥራ በትጋት እየተከናወነ መሆኑን የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ አስታውቀዋል፡፡

ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ ከሚቻልባቸው ስልቶች ግብይትን በደረሠኝ ማስደገፍ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ደረሠኝ የመቁረጥ ግዴታ በሕግ የተደነገገባቸው ነጋዴዎች ይህን መተግበር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ይህን በማይተገብሩ ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው፤ ለአብነትም 1 ሺህ 445 መርካቶ የሚገኙ ነጋዴዎች ከደረሠኝ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከማስጠንቀቂያ እስከ 100 ሺህ ብር ተቀጥተዋል ሲሉ ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡

በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ምክንያት ከንግድ እራሳቸውን አግልለው የነበሩ መመለሳቸው፣ ደረሠኝ የሚቆርጡ ነጋዴዎች ቁጥር መጨመሩ፣ የገቢ አሳሰብ እና ሕግ የማስከበር አቅም እያደገ መሆኑ የደረሠኝ ቁጥጥሩ ተጨባጭ ውጤት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ደረሠኝ መቁረጥ የሚጠበቅባቸው ያለመቁረጥ፣ ሐሰተኛ ደረሠኞችን መጠቀም፣ ደረሠኝ ሲቆርጡ ከግብይት በታች ገንዘብ መጻፍ፣ ዕቃ የማሸሽ፣ ከሕግ ለማምለጥ በሚል በድብብቆሽ ግብይት የመፈጸም ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይህን ታሳቢ በማድረግ ችግሩ በሚታይባቸው የተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በሌሊት ጭምር የቁጥጥር እና ክትትል ሥራ በጥብቅ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.