የሃይማኖት ተቋማት ትብብርና አብሮነት ለሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና እንዳለው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሃይማኖት ተቋማት ትብብርና አብሮነት ለሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና አለው ሲሉ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
ከኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጋር ትውውቅ ያደረጉት ሚኒስትሩ፤ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳይ ሰላማዊና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ አስተዋፆ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ትብብርና አብሮነት ለሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል የሰላም ግንባታ ስራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተው፤ የሰላም ሚኒስቴር በትብብርና በቅንጅት ከካውንስሉ ጋር ለመስራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡
የካውንስሉ ፕሬዚዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከመገፋፋት ይልቅ በመተባበር እና በመደጋገፍ ለሀገራችን ሰላም መረጋገጥ ሃይማኖቶች ትልቅ አቅም ሊሆኑ እንደሚገባ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡