Fana: At a Speed of Life!

በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ ህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የሚገኙ ህዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሎቹ ሰላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮዎች አስታወቁ።

በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ባለው የሰላም ሁኔታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም መንገሻ እንደገለፁት፥ የክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላም መሻሻል አሳይቷል።

የፀጥታ ኃይሉ ከማህበረሰቡ ጋር ባደረገው የተቀናጀ ጥረትም በየአካባቢው ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ገልጸው፤ የሰፈነውን ሰላም በማጽናት የህዝቦችን የልማት ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ተግባራት በትኩረት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኃይሌ ጉርሜሳ በበኩላቸው፥ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ጠንካራ ትስስር እንዳለው ገልጸዋል።

በአዋሳኝ አካባቢዎቹ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የተደረገውን የሰላም ሥምምነት ተከትሎ ከቄለም ወለጋና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም ከሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ መርጠው ወደ ካምፖች መግባታቸው ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.