የጎብኝዎችን ቆይታ ለማራዘም …
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም መስህብ ብዝኃነት እና ስብጥር የጎብኝዎች የቆይታ ጊዜ እንዲረዝም የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው በቱሪዝም ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት እና የቱሪዝም ባለሙያው ቴዎድሮስ ደርበው ገልጸዋል።
የጎብኝዎች የቆይታ ጊዜን በተመለከተ ከፋና ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት የቱሪዝም ባለሙያው ኢትዮጵያ ብዝኃነት ያለው የታሪክ፣ የባህል፣ የተፈጥሮ፣ የቅርስና የመልከዓ ምድር የቱሪዝም መስህብ ስብጥር ያላት አገር መሆኗን አስረድተዋል።
ሀገሪቱ ያላት የብዝኃነት ስብጥሩ ከፍ ያለ የቱሪዝም ሃብት የረዘመ የጎብኝዎች የቆይታ ጊዜ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
የቱሪዝም የቆይታ ጊዜ አንድ ጎብኝ ወደ መዳረሻው በሚገባበት ዕለትና በሚመለስበት ቀን መካከል ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሲሆን ፥ ይህም በዘርፉ ቁልፍ መለኪያ መሆኑን ባለሙያው አብራርተዋል።
የቱሪስቱ ፍላጎት፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ በመዳረሻው ያሉ እንደ መሰረተ ልማት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የቱሪዝም ባለሙያዎች ክህሎት፣ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ፣ የቱሪዝም ምርት ስብጥር፣ ለቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ መርዘምና ማጠር ቀጥተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የቱሪዝም ባለሙያው ቴዎድሮስ አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያን የቱሪስት የቆይታ ጊዜን አስመልክተው ሲያብራሩ እ.ኤ.አ በ2019 በተጠና ጥናት መሰረት ቆይታው 12 ነጥብ 5 ቀናት መሆኑንና ፥ ይህም ከቀጣናው አገራት የተሻለ የሚባል አሃዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የተሳለጠ የመጓጓዣ አገልግሎት መኖሩ፣ የጉዞ አሰራሮችና መስፈርቶች እየቀለሉ መምጣታቸው እና የጊዜ ውስንነት ያላቸው ጎብኝዎች መብዛት በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎብኝዎች የቆይታ ጊዜ እንዲቀንስ ምክንያት እየሆኑ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመጭዎቹ ወራት የገና፣ ጥምቀትና የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን የምታስተናግድ ሲሆን ኃይማኖታዊ በዓላትን ለመታደም እንዲሁም ለስብሰባ የሚመጡትን የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቆይታ የተራዘመና የሰመረ ለማድረግ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ተሳታፊዎች የቢዝነስ ጎብኝዎች ቢሆኑም ቢዝነስና መዝናኛን ያጣመረ ቱሪዝም እያደገ መጥቷል ብለዋል። በዚህም የተሳታፊዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ሁነቶችን በማዘጋጀት እንዲሳተፉ እንዲሁም በአዲስ አበባ እና አቅራቢያ ያሉ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ መስህቦችን እንዲጎበኙ የማድረግ ተግባር በስፋት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
የገና እና የጥምቀት በዓልን ለመታደም የሚመጡ ጎብኝዎችን በተመለከተ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶቹን ከማስጎብኘት በተጨማሪ ጎብኝዎች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ የጥቅል አማራጮችን በማዘጋጀት ቆይታቸውን አይረሴ ማድረግ ተገቢ እንደሆነም አስረድተዋል።
አስጎብኚ ድርጅቶችና ባለሙያዎች፣ ሆቴሎችና ሪዞርቶች እንዲሁም በቱሪዝም የአገልግሎት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት የተሳለጠና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት የቱሪዝም ባለሙያው ፥ መንግስትም ሚናውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የተራዘመ የጎብኝዎች ቆይታ ገቢን ከማሳደግ አንጻር ቀጥተኛ አስተዋፅኦ ያለው ሲሆን ዘላቂ የሆነ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲፈጠር የዘርፉ ተዋንያን ተባብረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በቴዎድሮስ ሳህለ