እንደ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ያሉ ታሪካዊ ምልክቶች የሀገርን ዓለም አቀፍ ገፅታ ለማሳደግ ሚናቸው የጎላ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ያሉ ታሪካዊ ምልክቶች የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገፅታ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስገነዘበ፡፡
የታደሰው ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት፣ ባሕላዊ ቅርስን ለኢኮኖሚ እድገት አስትዋጽኦ አድርጎ ቅድሚያ የሚሰጠውን የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ዕቅድን በማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡
በአንድነት ፓርክ የስኬት ሥራ እና በከተሞች የመስኅብ መዳረሻዎችን ከማሳደግ አኳያ በታየው ፍላጎት ላይ በመመርኮዝ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን እንደሚስብ ይታመናል ብሏል።
የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ በማሳደግ ገቢን ይጨምራል ያለው ጽሕፈት ቤቱ÷ በቱሪዝም አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለትም የሥራ እድል ፈጠራን እንደሚያሰፋ አስረድቷል፡፡
እንደ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ያሉ ታሪካዊና ባሕላዊ ምልክቶች የከተማ ልማትን በማነሳሳት እና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገፅታ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ነው ያለው፡፡