Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ ከኢትጵያ ጋር ያላት ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ቱርክ ታሪካዊ ወዳጅነት በሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር መስኮች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር በርክ ባራን ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ቱርክ ወዳጅነት ቡድን በሀገራቱ የተለያዩ የትብብር መስኮች ተወያይቷል።

ውይይቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር በርክ ባራን፥ በኢትዮጵያና ቱርክ መካከል ያለው ታሪካዊ ወዳጅነት በሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ መስኮች የተቆራኘ ነው ብለዋል።

በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ጤና፣ በባህልና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መስኮችም የሀገራቱ ትብብር መሰረት እንደሆኑ አስረድተዋል።

በቀጣይም የሀገራቱን ዘመን ተሻጋራ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ትብብር በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቱርክ አቀራራቢነት በኢትዮ-ሶማሊያ መካከል የተደረሰው ስምምነትም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝነት ያለው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል አምባሳደሩ።

የኢትዮ-ሶማሊያ ስምምነትም የሀገራቱን ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም በአድናቆት መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.