Fana: At a Speed of Life!

295 የሚሆኑ አዳዲስ የቴሌኮም ማስፋፊያዎች በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ተደረጉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ባለፉት ጥቂት ዓመታት 295 የሚሆኑ አዳዲስ የቴሌኮም ማስፋፊያዎችን በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ አድርገናል ሲሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ እንቅስቃሴን የገመገመ ሲሆን÷ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ የቴሌኮም አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ የኃይል አቅርቦት መሆኑን ጠቁመው በገጠር ያሉ የቴሌኮም ጣቢያዎችም ሶላርንና በከፊል ጀነሬተርን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እስካሁን 3 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር በቴሌ ብር መተግበሪያ ዝውውር መፈጸሙንም ተናግረዋል፡፡

240 ሺህ የሚሆኑ ነጋዴዎችም ክፍያቸውን በቴሌ ብር እየፈጸሙ መሆኑን በማንሳት ይሄም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋጽኦ እያደረገ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን በማቅረብ ሕይወትን ማቅለል እንዲሁም የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በመላ ሀገሪቱ 1 ሺህ 33 የሚሆኑ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዲሁም ቴሌ ገበያና ቻት ቦት የተሰኙ የኦንላይን አገልግሎት መስጫ አማራጮች ያሉት ቴሌ ብር የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ያቀላጠፈና ያዘመነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ካሉና ለደንበኞች አገልግሎት ከሚሰጡ 195 ኦፕሬተሮች የኢትዮ ቴሌኮም ከናይጀሪያ ቀጥሎ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 1 ሺህ 298 ተጨማሪ የሞባይል ጣቢያዎችን ለመገንባት መታቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አመላክተዋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.