Fana: At a Speed of Life!

የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በሰራባ ተሐድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል አቀባበል ተደረገላቸው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ አም ሲ) የመንግሥትንና የሕዝብን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በሰራባ ተሐድሶ ማሰልጠኛ ማዕከል አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ታጣቂዎቹ የክልሉ ሕዝብ በዚህ ግጭት ያተረፈው ሞትና ውድመት መሆኑን በመረዳታቸው የሰላም ጥሪውን መቀበላቸውን ተናግረው፤ የበደልነውን ሕዝብና ለመካስ ዝግጁ ነን ብለዋል።

በጦርነት የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ መገንዘባቸውን ገልጸው፤ በትጥቅ ትግል የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችንም ጥሪውን መቀበል አለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአቀባበሉ ላይ የተገኙት የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው እንዳሉት፥ የክልሉን ሕዝብ ሰላም ለማድረግ የመንግሥትንና የሕዝብን ጥሪ መቀበላችው የሚመሰገን ነው።

በቀጣይም ሰላም እንዲመጣና ህዝቡ ወደ ቀደመ ልማቱ እንዲመለስ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሰላም ጥሪን የተቀበሉ የታጠቁ ኃይሎች በጭልጋ ሰራባ ካምፕ ትጥቃቸውን ለመንግሥት ማስረከባቸውን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሁን መንግሥቱ ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ የክልሉን ሕዝብ ልማት ለማሳደግ እንዲሠሩ የተሐድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው የሥራ እድል እንደሚፈጠርላቸውም ገልጸዋል።

አቶ በሪሁን የታጠቁ ኃይሎች የሰላም ጥሪውን መቀበላቸው የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ ያደርጋል ማለታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.