Fana: At a Speed of Life!

አትሌት በሪሁ አረጋዊ የ10 ኪሎ ሜትር ክብረ ወሰንን ሰበረ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በስፔን ማድሪድ በተካሄደ ሳን ሲልቬስተር 2024 የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት በሪሁ አረጋዊ አዲስ ክበረወሰን በመስበር አሸንፏል፡፡

አትሌት በሪሁ ርቀቱን 26 ደቂቃ ከ32 ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ ነው ክብረ ወሰን በማሻሻል ያሸነፈው፡፡

ኡጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ በአንድ ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ÷ ስፔናዊው አዴል ሚካኤል ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል፡፡

የ10 ኪሎ ሜትር ክበረ ወሰን በኬንያዊው አትሌት ሮኔክስ ኪፑሩቶ ተይዞ የነበረ ሲሆን÷ አትሌቱ የአበረታች ንጥረ ነገር መጠቀሙን ተከትሎ ውጤቱ መሰረዙ ይታወቃል፡፡

በተመሳሳይ በጣልያን ቦላንዞ ከተማ በተካሄደው ዓመታዊው የቦክላሲክ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ጥላሁን ሃይሌ አሸንፏል፡፡

ጥላሁን ርቀቱን በ27 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ በመግባት ሲያሸንፍ÷ትውልደ ኢትዮጵያዊው እና ለጣልያን የሚሮጠው የማነ ከሪፓ ሁለተኛ እንዲሁም ኬንያዊው ቻርለስ ሮቲች 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡

በተመሳሳይ በጣልያን ቦላንዞ ከተማ በተካሄደ የሴቶች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት አለኸኝ ባወቀ 15 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.