Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አገልግሎትን ለማስፋፋት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

አዲስ አበባ እና ጎንደር ከተማ አሥተዳደሮች በብዙኃን ትራንስፖርት ደረጃ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት መጀመራቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሀሰን ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም በድሬዳዋ፣ ሐረር እና ጅግጅጋ ከተሞች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የኃይል መሙያ (ቻርጀሮች) ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሁኔታው በነዳጅ የሚሠሩ የብዙኃን፣ የመንግሥት ተቋማት እና የታክሲ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ በሚሠሩ የመቀየር ፍላጎት መኖሩን ጠቁመው÷ አሁን ላይ በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በ10 ዓመታት ውስጥም ከ432 ሺህ የሚልቁትን በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክ ለመተካት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል፡፡

እስከ አሁን በተከናወነ የሁለት ዓመት ተኩል ሥራም እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አገልግሎት መሥጠት የሚችሉ ሆነው ያረጁ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ እንዲሠሩ የማሻሻል (ሞዲፊኬሽን) ሥራ ለማከናወን የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኗን አስገንዝበው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚነትን ማጎልበት÷ የከባቢ አየር ብክለትን በመቀነስ ጤናማ ትውልድ እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር ለነዳጅ ድጎማ የሚወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ለሌላ ልማት ማዋል እንዲቻል ይረዳል ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.