Fana: At a Speed of Life!

በ2017 በጀት ዓመት የተጠናከረ ዕድገት እንደሚኖር ይጠበቃል-ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘንድሮው በጀት ዓመት የተጠናከረ ዕድገት እንደሚኖር ይጠበቃል ሲል ብሔራዊ ባንክ ገለፀ፡፡

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል፡፡

 

ስብሰባውን አስመልክቶ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

ባንኩ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከባንኩ ዋጋን ከማረጋጋት ቀዳሚ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያቀርባል፣ ያስጸድቃል፡፡

 

በዚህ ረገድ  ኮሚቴው የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ አዝማሚያዎችን፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል፡፡

ኮሚቴው ከእነዚህ ማክሮ ኢኮኖሚአዊ ግምገማዎችና ከቅርብ ጊዜ የወደፊት እይታዎች አጠቃላይ ግምገማ በመነሣት በገንዘብ ፖሊሲው ተግባራዊ የሚደረጉ ተገቢ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ዝርዝር የፖሊሲ እርምጃዎች በተመለከተ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡

 

በዚሁ መሠረት፣ ኮሚቴው በቅርብ ጊዜ በተከሰቱ የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ የተወያየ ሲሆን፣ በውይይቱ ያካተታቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-

 

የዋጋ ግሽበት፡- ኮሚቴው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በህዳር ወር 2017 መጨረሻ 16.9 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገበው አሃዝ ዝቅተኛው ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው፣ ከምርታማነት ባሻገር ብሔራዊ ባንክ ከነሐሴ 2015 ጀምሮ ተግባራዊ ባደረገው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ምክንያት ነው፡፡

 

ምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት አሁንም ከፍተኛና 18.5 በመቶ ቢሆንም፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ግን የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ በአንጻሩ፣ በቅርቡ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥና በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ የተደረገው አስተዳደራዊ የዋጋ ማሻሻያ ምግብ ነክ ላልሆነ የዋጋ ግሽበት መጨመር የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

 

በመሆኑም፣ ምግብነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ባለፈው ወር ከነበረው 11.6 በመቶ ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ በማሳየት በህዳር ወር 2017 መጨረሻ 14.4 በመቶ ሆኗል፡፡

 

እንዲሁም ህዳር ወር 2017 ላይ 0.8 በመቶ ከዜሮ በታች የሆነ ወርሃዊ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ይህም የወቅቱን ሁኔታና እስካሁን ድረስ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ያመጣው ጫና ውስን መሆኑን አመላካች ነው፡፡

 

ዕድገትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፡- በ2016 በጀት ዓመት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 8.1 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ በዘንድሮው በጀት ዓመትም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ክፍሎች የታየው ጥሩ የዝናብ ወቅትና በግብርናው ዘርፍ የተወሰዱ በርካታ የአቅርቦት ውጥኖች በዘንድሮው የሰብል ዘመን ከፍ ያለ ምርት እንደሚመዘገብ ያመለክታሉ፡፡

 

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት የተመዘገበው የመብራት ኃይል ምርትም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍ ያለ ዓመታዊ የምርት ዕድገት እንደሚኖር ይጠቁማል፡፡ የአየር ትራንስፖርትና የቱሪስቶች ፍሰትም የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገትን እንደሚደግፍ ይጠበቃል፡፡በጥቅሉ፣ አብዛኞቹ አመልካቾች እንደሚያሳዩት፣ በ2017 በጀት ዓመት የተጠናከረ ዕድገት እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

 

የገንዘብ አቅርቦት ሁኔታ፡- በ2016 በጀት ዓመት ቁልፍ በሚባሉት የገንዘብ ዝውውር አመልካቾች (broad money aggregates) ረገድ ከፍተኛ ቅናሽ መታየቱንና ይህም ለዋጋ ግሽበት ጫናና ለግምታዊ አስተሳሰብ መርገብ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ኮሚቴው አስተውሏል፡፡ እንዲሁም፣ ከበጀት ዓመቱ ጅማሮ ወዲህ በሁሉም የገንዘብ ዝውውር አመልካቾች ዘንድ በመጠኑ ከፍ ያለ ዕድገት ታይቷል፡፡ ለምሳሌ፣ እስከ ህዳር 2017 ድረስ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) የ20 በመቶ፣ መሠረታዊ ገንዘብ (base money) ደግሞ የ17በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ሲያሳዩ፣ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ብድር ደግሞ በ19 በመቶ ጨምሯል፡፡

 

ይሁን እንጂ፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት ቢኖርም፣ ከኢኮኖሚው ስፋት አንጻር የገንዘብ ዝውውር አመልካቾች የመቀነስ አዝማሚያ ታይቶባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ የጠቅላላ ገንዘብ፣ የመሠረታዊ ገንዘብ እና የሀገር ውስጥ ብድር ዕድገት የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ካላደረገው የጠቅላለ የሀገር ውስጥ ምርት (nominal GDP) ዕድገት ያነሰ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ማስተካከያ ማድረግ ለመካከለኛ ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ ሁኔታ ነው፡፡

 

የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት፡- የባንክ ሥርዓት ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር፣ ከፍ ያለ የመጠባበቂያ ሂሳብና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ እንደሆነ በኮሚቴው ተገምግሟል፡፡ ከዚሁ ጋር፣ ባንኮች እርስ በርስ የሚገበያዩበት የገንዘብ ገበያ የተጀመረ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ባንኮች ዘንድከፍ ያለ የጥሬ ገንዘብ አከል ንብረት (liquidity) እጥረት ተከስቷል፡፡ ይህም በግል ባንኮች ዘንድበሚታየው ከፍተኛ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ ጥምርታ (oan to deposit ratio) እንዲሁም በዝቅተኛ ትርፍ ተቀማጭ ሂሳብ (excess reserve) ጥምርታ ተንጸባርቋል፡፡ እነዚህ የጥሬ ገንዘብ

አከል ሀብት ችግሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥራ ላይ በዋሉ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያና በብሔራዊ ባንክ የአንድ ቀን የብድር አገልግሎት መፍትሔ እያገኘ ነው፡፡

 

የፊስካል ሁኔታ፡- የበጀት እንቅስቃሴዎች ጥሩ አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ ይህም በዘንድሮው በጀት ዓመት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወሰድ ያደረገና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በእጅጉ የሚደግፍ ሆኗል፡፡

 

የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፡- ሐምሌ 2016 በተወሰደው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ለውጥ የተነሣ የውጭ ንግድ ዘርፍ ትልቅ መሻሻል እያሳየ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የወጪ ንግድና ሐዋላ ከፍተኛ ዕድገት ሲያሳዩ፣ የገቢ ንግድ ግን መጠነኛ ቅናሽ ታይቶበታል፡፡ በአንጻሩ፣ ከግልና ከመንግሥታዊ ምንጮች ወደ ሀገር ውስጥ የፈሰሰው የካፒታል መጠን ጨምሯል፡፡

ስለሆነም፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት የከረንት አካውንት ትርፍ ተመዝግቧል፤ የንግድ ባንኮችም ሆነ የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡

 

ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች፡- የዓለም ኢኮኖሚ የሀገር ውስጥ ሁኔታዎችን የሚነካው በዋናነት በሸቀጦች ዋጋ አማካይነት ሲሆን አሁን ያለው የሸቀጦች ዋጋ በጥቅሉ ለሀገራችን ምቹ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ የነዳጅ ዋጋ የበጀት ዓመቱ ከተጀመረ ወዲህ 15 በመቶ ቀንሷል፡፡ በአንጻሩ፣ የዋና ዋና የወጪ ምርቶች ዋጋ (ማለትም የቡናና የወርቅ) ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ለውጭ ክፍያ ሚዛን መሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አንዳንድ የዓለም ኢኮኖሚ ክፍሎች (ለምሳሌየኢትዮጵያን የንግድ አጋሮች ጨምሮ) የዕድገት መቀዛቀዝ ቢታይባቸውም፣ ሁኔታው በውጭቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ገና ጉልህ ተጽእኖ አላሳደረም፡፡

 

እንዲሁም፣ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ የሚታዩ አንዳንድ አዎንታዊ ውጤቶች፣ ለምሳሌ ያደጉ ሀገራት የገንዘብ ፖሊሲዎቻቸውን ማለዘባቸው፣ እስካሁን በሀገራችን ላይ ያሳደሩት ተጽእኖ ውስን ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ከውጭውዓለም ጋር ያላት የንግድና የፋይናንስ ትስስር አሁንም ቢሆን ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡

 

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ግምገማና ውሳኔ

 

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ የቅርብ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ አበረታችና በጥቅሉ የመርገብ አዝማሚያ ቢያሳይም፣ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቧል፡፡ በተለይም፣ የዋጋ ግሽበት አሁንም ቢሆን ከፍተኛና በመካከለኛ ጊዜ ሊደረስበት ከታሰበው የባለአንድ አሃዝ ግብ በላይ መሆኑን ኮሚቴው አስተውሏል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ፣ በኮሚቴው አመለካከት፣ ጠንቃቃ የገንዘብ ፖሊሲ መከተልን አስፈላጊ የሚያደርጉ ሁለት ማክሮ ገጽታዎች አሉ፡፡ እነርሱም፣ በሚቀጥሉት ወራት የፊስካል ሁኔታዎችን ለማላላት ያለው ፍላጎት (መደበኛ የበጀት አፈጻጸም ዑደት ለመከተልና ለደሞዝ፣ ለማህበራዊ ኑሮና ለሴፍቲኔት የሚደረገውን ወጪ ለማሳደግ ያለው ዕቅድ) እና ከተጣራ የውጭ ምንዛሪ ፍሰት ዕድገት ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል መጠነኛ የገንዘብ ዕድገት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች በመነሣት፣ ኮሚቴው ከቅርብ ወራት ወዲህ ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት መርገብ (በህዳር ወር 2017 የ0.8 በመቶ ቅናሽ ከዜሮ በታች)፣ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ከተለመደው ውጭ የሆነ ጥብቅ የጥሬ ገንዘብ አከል ሀብት (liquidity) እና የብድር ሁኔታ እንዲሁም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት አንጻር ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ቅናሽ መኖሩን ተገንዝቧል፡፡ ኮሚቴው እነዚህን ሁኔታዎች በማመዛዘን፣ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ቢኖሩም አሁን ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ማስቀጠል እንደሚገባ አስተውሏል፡፡

 

ከዚህ እይታ በመነሣት ኮሚቴው የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

አንደኛ፣ አሁንም ቢሆን ከፍ ብሎ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመን መኖሩን ለማረጋገጥ ሲባል የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (monetary policy rate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ፡፡

 

ሁለተኛ፣ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደር ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር ገና በመሆኑ፣ የባንክ ብድር ዕድገት ግብ የመጠቀም ሁኔታ እንዲቀጥል፣ ነገር ግን ለዚህ በጀት ዓመት የብድር ዕድገት ግቡ ከ14 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል፡፡

 

ሶስተኛ፣ በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በሚሰጣቸው የአንድ ቀን የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት (standing deposit facility)፣ በአንድ ቀን የብድር አገልግሎት (standing lending facility) ላይ የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሂሳብ በነበረበት እንዲቆይ ተወስኗል፡፡

 

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ቀጣይ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎች በቀጣይ ወራት በሚከሰቱ የዋጋ ግሽበት ውጤቶች ግምገማ ላይ የተመሠረቱ እንደሚሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ቀጣዩ የኮሚቴው ስብሰባ መጋቢት 16 ቀን 2017እንዲሆን ተወስኗል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.