የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ 116ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ 116ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እያከበረ ነው።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በውድድሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት የፌዴራል ፖሊስ ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያን ስፖርት በመገንባት ረገድ ስሙ በጉልህ የሚነሳ ነው።
ፌዴራል ፖሊስ 116ኛ የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር የፖሊስ መደበኛ ተግባር ከሆነው ወንጀል መከላከል ባለፈ ለሀገሪቱ የስፖርት ዕድገት የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን የሚቀጥል ይሆናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በተጨማሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድን እንዲሁም የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በስፖርታዊ ውድድሩ መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል።
በዓሉ ሲከበር እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ አትሌትክስ፣ ጠረጴዛ ቴንስና ገመድ ጉተታ ውድድር የሚካሄድባቸው የስፖርት ዓይነቶች ሲሆኑ ስፖርታዊ ውድድሮቹ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆዩ ተገልጿል።