Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ ህወሓት ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)  ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ አሳሰበ፡፡

 

በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

 

ህወሓት በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሠረት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡ ይታወቃል።

 

በአዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 3 መሠረት በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ ፓርቲ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ያዛል።

 

ቦርዱም የፓርቲውን በልዩ ሁኔታ መመዝገብ ባሳወቀበት ነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ቁጥር አ1162/11/15180 በግልፅ እንዳስቀመጠው ፓርቲው ይህው ደብዳቤና የምዝገባ ሰርትፊኬት ከደረሰው አንስቶ ባሉት ስድስት ወራቶች ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባውን ማድረግ አንዳለበት አስታውቋል።

 

በሌላም በኩል አዋጅ ቁጥር 1332/2016 ዓ.ም ለማስፈፀም ባወጣው መመሪያ ቁጥር 25/2016 አንቀፅ 12 መሰረት በተጠቀሰው አዋጅ መሰረት በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ የፖለቲካፓርቲ ምዝገባውን ካገኘበት ጊዜ አንስቶ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እንዳለበት ያዛል።

 

ፓርቲው ከፍ ብሎ የተመለከተውን የአዋጁንና የመምሪያውን ድንጋጌዎችና ቦርዱ ልዩ ምዘገባ ሰርትፊኬቱን ሲሰጠው በፃፈው ደብዳቤ ላይ የተገለፀውን በስድስት ወር ውስጥጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ የሚለውን ግዴታ ያለተጨማሪ ማሳሰቢያ መፈፀም እንዳለበት የሚታመን ቢሆንም ቦርዱ ለፓርቲው ነሀሴ 3 ቀን በቁጥር 1162/11/15180፣ ነሀሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/15209 እና ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም በቁጥር አ1162/11/15278 በፃፋቸው ደብዳቤዎች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማከናወን ጠቅላለ ጉባኤውን እንዲያደርግ አስታውቋል፡፡

 

ፓርቲው በልዩ ሁኔታ የተመዘገበው ነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም በመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤውን እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም እንዲያደርግ ይጠበቃል። በሌላ በኩልም ለዚሁ የጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት የሚያስፈልገውን የቅድመ ጉባኤ ዝግጅት የተመለከቱ ስራዎችን ቦርዱመከታተል እንዲችል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት ጉባኤው የሚደረግበትን ቀን ለቦርድ እንዲያሳውቅ የሚጠበቅ ነው። ይሁንና ይህ ደብዳቤ አስከተፃፈበት ቀን ድረስ ፓርቲው ከተመዘገበ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ቦርዱ አያውቅም።

 

በመሆኑም ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበበት ከነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ የሚገባው ወቅት ሊገባደድ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ የቀረው በመሆኑ ፓርቲው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በልዩ ሁኔታ በተመዘገበበት አዋጅ፣ አዋጁን ለማስፈፀም የወጣው መመሪያና ቦርዱ ከነሀሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ ጊዜ ለፓርቲው በፃፈው ደብዳቤዎች ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች በማክበር በቀረው አጭር ጊዜ የጠቅላላ

ጉባኤውን እንዲያደርግ ቦርዱ በጥብቅ ያስታውቃል።

 

ይህ በሕግ ፓርቲው ላይ የተጣለ ግዴታ በወቅቱ ሳይፈፀም ቢቀር ቦርዱ ሕጉን መሠረት በማድረግ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ከወዲሁ በአክብሮት ያስገነዝባል።

 

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.