ወቅታዊ ጉንፋን እና ጉንፋን መሰል የመተፈንሻ አካላት ህመም መንስኤ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጉንፋን ሕመም በተፈጥሮ የላይኛውን የመተንፈሻ የሰውነት ክፍሎች ማለትም አፍንጫ፣ ጎሮሮ እና የአየር መተላለፊያ ቧንቧን የሚያጠቃ ተላላፊ ሕመም ነው።
‘ሪኖ ቫይረስ’ ለጉንፋን መከሰት ዋና ምክንያት ሲሆን÷ ኮሮና፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ፓራ ኢንፍሉዌንዛ፣ አር ኤስ ቪ (RSV) ቫይረሶች ደግሞ ለጉንፋን እና መሰል ህመሞች መከሰት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
ከተጠቀሱት ቫይረሶችም ለጉንፋን ሕመም መከሰት 50 በመቶ ድርሻውን የሚይዘው ሪኖ ቫይረስ መሆኑ ይነገራል፡፡ በደረቅና ነፋሻማ ወቅት የአፍንጫ የውስጠኛው ስስ ሽፋን “ሙከስ መምብሬን” ስለሚደርቅ የጉንፋን ሕመም እና ተላላፊነቱ እንደሚጨምሩ በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡
የክረምት ወራት ወይም የዝናብ ወቅት ማብቃቱን ተከትሎ መስከረምን ጨምሮ በጥቅምትና ኅዳር ወራት እንደዚህ አይነት ጉንፋን መሰል ህመም የሚጠበቅ መሆኑም ይነገራል፡፡
ሕመሙ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው በሚያስልበት ወይም በሚያስነጥስበት ጊዜ እንደሆነና በተጨማሪም ሰዎች ቫይረሱ ያረፈበትን የበር እጀታ፣ጠረጴዛ ወይም በሕመምተኛው የተነካካን ሰው እጅ ከነኩ በኋላ አፋቸውንና አፍንጫቸውን ሲነካኩ ቫይረሱ ለመተላለፍ በሚፈጠርለት ምቹ ሁኔታ መሆኑን የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ መረጃ ያሳያል።
የጉንፋን ሕመም አብዛኛውን ጊዜ እስከ ሁለት ሳምንት ሊቆይ እንደሚችልም የተገለፀ ሲሆን÷ከምልክቶቹ መካከልም የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ ራስ ምታትና ጉሮሮን መከርከር፣ ማስነጠስ፣ አይን ማሳከክ እና መቅላት፣ ማስታወክ፣ ከፍ ሲልም የትንፋሽ ማጠር፣ ከፍተኛ ድካምና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ይጠቀሳሉ።
አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ በሽታው የመዛመት እድሉ ከፍ ሊል እንደሚችል በተለይ ቀዳሚ ተጎጂ የሚሆኑት ህጻናትና አረጋዊያን መሆናቸውንም መረጃው ይጠቁማል፡፡ እንደ አስም፣ የስኳር በሽታ፣ ካንሰር እና ሌሎች ሥር የሰደዱ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያሉባቸው ሕሙማን ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉና ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራና ህክምና ሊያደርጉ እንደሚገባ ይመከራል፡፡
በተጨማሪም የጉንፋን ሕመም የጆሮ ኢንፌክሽን እና የሳንባ ምች ሕመምን ጨምሮ ለተለያዩ ሕመሞች ተጋላጭ ሊያደርግ እንደሚችልም ይታመናል፡፡
የእጅ ንጽህናን መጠበቅ፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ የአፍና አፍንጫ ጭምብል ማድረግ፣የምንጠቀምባቸውን በአካባቢዎቻችን የሚገኙ ቁሳቁሶችን ማጽዳት እና የብዙሃን ማጓጓዣ ትራንስፖርት ላይ መስኮቶችን በመክፈት በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በማድረግ በሽታውን መከላከልና የመተላለፍ ዕድልን መቀነስ እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡
የበሽታው ምልክት የሚታይበት ሰው በፍጥነት በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን የህክምና ምክር እና ዕርዳታ ማግኘት እንዳለበትም ይመከራል፡፡