የኢትዮጵያ ክለቦች አትሌቲክስ ሻምፒዮና መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ክለቦች የአጭር፣ መካከለኛ፣ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የርምጃ እና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ዛሬ በተካሄደው የሴቶች የርዝመት ዝላይ የፍፃሜ ውድድርም÷ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት ፓች ኡመድ 5 ነጥብ 95 ሜትር በመዝለል አንደኛ ሆናለች፡፡
በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5 ነጥብ 87 ሜትር በመዝለል አትሌት አርያት ዴቪድ ሁለተኛ እንዲሆም ከሸገር ሲቲ 5 ነጥብ 77 ሜትር በመዝለል አትሌት አስቴር ቶሎሳ 3ኛ ደረጃን መያዝ ችለዋል፡፡
አሸናፊዎቹም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስኅን ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡
ሌሎች የማጣሪያና የፍፃሜ ውድድሮች መካሄዳቸውን እንደቀጠሉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡