አማካይ የቡና ምርታማነት በሄክታር 8 ነጥብ 5 በመቶ ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና ምርታማነትን በማሻሻል ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የቡና ምርት ትመና እንዲሁም የቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም ልማት ፓኬጅ ሰነድ ምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ እንደገለፁት÷ባለፉት ሶስት ዓመታት የቡና ምርታማነት ለመጨመር በተከናወኑ የሪፎርምና የንቅናቄ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል።
ከቡና ምርት አሰባሰብና ገበያ ድረስ ባለው ሂደት ላይ በተከናወኑ ተግባራት በኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
“በአርሶአደሩ፣ በባለሙያውና በአመራሩ ዘንድ የነበረውን የአመለካከትና የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት የቡና ምርታማነት ላይ ለውጥ አምጥተናል” ሲሉም አክለዋል።
ያረጁ የቡና ዛፎች ጉንደላና ነቅሎ በአዲስ በመትከል ረገድ በተከናወነ ስራ ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ ጠቁመው÷ አማካይ የቡና ምርታማነትን በሄክታር ወደ ስምንት ነጥብ አምስት በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በኦሮሚያ ንግድ ቢሮ የቡና ግብይት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ በንቲ በበኩላቸው÷ ከአርሶአደሩ ጀምሮ እስከ ግብይት ድረስ በተሰራው ስራ የቡና ምርታማነት መሻሻሉን ተናግረዋል ።
በክልሉ በቡና ዛፍ ጉንደላና በነቅሎ ተከላ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው÷በክልሉ ምርታማነቱን በአማካኝ በሄክታር ከሰባት ነጥብ አምስት ኩንታል ወደ ዘጠኝ ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ እንደገለፁት÷ በጫካ፣ በከፊል ጫካ፣ በጓሮና በዘመናዊ ቡና ልማት ላይ በክልሉ የተሻለ ስራ ተሰርቷል።
“በተለይ በተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ በአረም ቁጥጥርና ኩትኳቶ ላይ በመስራታችን በምርታማነት የተሻለ ውጤት አግኝተናል” ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ቡናና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቀሬ በበኩላቸው÷ በክልሉ በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ በተሰራ ስራ የተሻለ ውጤት መገኘቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተለይ በግብይትና ምርት አሰባሰብ አመራሩ፣ ባለሙያውና አርሶአደሩ “በቅንጅት የዘርፉን ሪፎርም ውጤታማ በማድረጋቸው የተሻለ ውጤት አግኝተናል ” ብለዋል ።