ብሔራዊ ቤተ መንግስት የድላችን እና የውጣ ውረዶቻችን ድርሳን የሚነበብበት መጽሃፍ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ ቤተ መንግስት ከፍ ያለ ኪናዊ ጥበብ የተላበሰ ህንጻ ብቻ ሳይሆን የታሪካችን መድብል፤ የተጋድሏችን የፈተናዎቻችን፣ የድላችን እና የውጣ ውረዶቻችን ድርሳን የሚነበብበት መጽሃፍ ነው ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በብሔራዊ ቤተ መንግስት የምረቃ መርሀ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በዚሁ ቤተ መንግስት የዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት መስተጋብር ጎላ ብሎ ይታያል ብለዋል።
የቆምንበት ስፍራ ከንጉሰ ነገስታዊ ስብሰባዎች እስከ ውስብስብ የዲፕሎማሲ ድርድሮች ድረስ አሻራ ያረፈበት ዛሬም ይታያል ሲሉ ገልጸዋል።
የቤተ መንግስቱ አዳራሽ በርካታ የአፍሪካ መሪዎችን እና ተጽእኖ ፈጣዎችን አስተናግዷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አፍሪካ የመጀሪያው አህጉራዊ ተቋም እንዲኖራት ያስቻለው በዚህ አዳራሽ የተደረገ ውይይት ነው ሲሉም አስታውሰዋል፡፡
ይህ ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስ ተጠብቆ ሲቆይ በኢትዮጵያ ታሪክ መዝገብ ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ የረጅም ጊዜ ቅርስ የመጠበቅ ባህል እንዳለን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህ ቤተመንግስተ በሚገባው መንገድ ታድሶ ለህዝብ እይታ ክፍት እንዲሆን ሲወስኑ የቤተ መንግስቱን ታሪካዊ እና ህያው ፋይዳ እንዲሁም ቅብብሎሽ ከፍ አድርገው መገንዘባቸውን ያሳይል ብለዋል፡፡
ታሪክ በቤተ መንግስት ካዝና ውስጥ ተቆልፎ የሚቀመጥ ሳይሆን ክፍት ሆኖ የምናየው የምናነበው የምንማርበት የምናደንቀው ከዛሬ ፍላጎታችን ጋር አስማምተን ዛሬ በምን እና እንዴት መገንባት እንዳለብን የምንረዳበት ነው ሲሉም አመላክተዋል፡፡
ዛሬ ዳግመኛ የተወለደው ይህ ቤተ መንግስት ለታካሪችን ድንቅ ምስክር ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ የቱሪስት መህስብ ፣ የዲፕሎማቲክ ተግባራት መከወኛ፣ የባህል ልውውጥ ማዕከል፣ የውይይት እና ትብብር መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
መጪው ትውልድ ከቀደሙት ሰዎች ውርስ ጋር የሚገናኝበት የታሪክ ሀብል እና ሰንሰለት ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ይህንን እውን ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ላደረጉት አስተዋጾ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቤተ መንግስቱ ዕድሳት መንግስታቸው ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።