የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎች ቁጥር 74 ሚሊየን ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሰራው ሥራ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚዎች ቁጥር 74 ሚሊየን መድረሱን የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
በለውጥ ዓመታቱ 25 ሚሊየን ገደማ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸው÷ በዚህም የተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 74 ሚሊየን ማደጉን ተናግረዋል፡፡
መንግስት የንጹህ ውሃ ተጠቃሚውን ህብረተሰቡ በከተማም ይሆን በገጠር አካባቢዎች ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማና ትልቅ ስኬት ያስገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በኢነርጂ ዘርፉ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸው÷ ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተከናወነውን ትልቅ ስኬት አንስተዋል።
በድርቅ እና በጎርፍ ይከሰት የነበረውን የአደጋ የተጋላጭነት ለመቀነስ መንግስት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ በትኩረት መሰራቱንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣናውን በሃይል ለማስተሳሰር ከፍተኛ ስራ እየሰራች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ÷ይህም ከራስ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተሰራው ስራ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።