የአውሮፕላን አደጋ መደጋገምና የአቪየሽን ኢንዱስትሪው …
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ልጅ መሻት ከኖረበት ቤት፣ መንደር፣ ሀገር እና ዓለም ብቻ ሊገደብ አለመቻሉን በየጊዜው ከሰማይ ረቅቆ የእንግዳ ፕላኔቶችን አድማስ ሲበረብር መታየቱ ማረጋገጫ ነው፡፡
ዓለምን ከሚያስደንቅ የሰው ልጅ ስኬቶች መካከል የሚጠቀሰው አውሮፕላን በፈረንጆች 1903 በራይት ወንድማማቾች ከተፈጠረ በኋላ የዓለምን ህብረተሰብ አኗኗር የቀየረ ነው፡፡ የሰውን ልጅ ኑሮ አቅልሎ ካሰቡበት ያደርሳል፡፡
ሆኖም ይህ ሣይሆን የሚቀርበት አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፤ በተለይም በዚህ ሰሞን በተደጋጋሚ የሚሰማው የአውሮፕላን አደጋ ብዙዎችን ካሰቡበት ያስቀረና የሀገራትን ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ አድርጎ ማቅ ያለበሰ ሆኗል፡፡
እንደአብነት ከቀናት በፊት 62 መንገደኞችንና አምስት ሰራተኞችን የጫነ ኢምብሬር 190 የተባለው የበረራ ቁጥር ጄ2-8243 አውሮፕላን በካዛኪስታን አክታው ከተማ አቅራቢያ መከስከሱ ይታወሳል፡፡ ከዚህ አደጋ በህይወት የተረፉ ቢኖሩም ብዙዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡
አውሮፕላኑ በሩሲያ ቼቺኒያ ከባኩ ወደ ግሮዝኒ ሲበር የነበረ ቢሆንም በግሮዝኒ ጭጋግ ምክንያት ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲዞር መደረጉ ተገልጿል በወቅቱ፡፡
ይህ በተከሰተ በቀናት ውስጥ 181 ሰዎችን ከታይላንድ ባንኮክ አሳፍሮ ደቡብ ኮሪያ የደረሰው አውሮፕላን ሙአን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር ተከስክሶ ሁለት የአውሮፕላኑ ሰራተኞች በህይዎት ቢተርፉም 179 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ሰምተናል።
ጀጁ የተባለ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ለማረፍ ሲሞክር ከአውሮፕላን ማረፊያ አጥር ጋር ተጋጭቶ አደጋው እንደደረሰም ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም የበረራ ቁጥር 2259 የሆነ ኤር ካናዳ አውሮፕላን በሃሊፋክስ ስታንፊልድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር አንደኛው ጎማ አልዘረጋ በማለቱ ተንሸራትቶ መስመር በመሳቱ በእሳት መያያዙም ተሰምቷል፡፡
ሆኖም 73 መንገደኞችና የበረራ ሰራተኞች በፍጥነት ከአውሮፕላኑ እንዲወጡ መደረጉም ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም በአርጀንቲና፣ ጊኒ፣ ሃዋይ እና ብራዚል የአውሮፕላን አደጋ ተከስቶ ብዙ ሰዎች ለህልፈት ተዳረገዋል፡፡
ይህም ተደጋጋሚ የአውሮፕላን አደጋ በዓለም የአቪየሽን ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ምርመራ ሊደረግበት እንደሚገባ እየተነሳ ነው፡፡
መሰል አደጋዎች ሲከሰቱ የአውሮፕላኑ የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) በመጠቀም ስለአደጋው ምርመራ ይካሄዳል፡፡
የአውሮፕላን አደጋ በብዛት የሚከሰቱበት ምክንቶች ውስጥ የአውሮፕላን ቁሳቁሶች (የመካኒካል) ችግር፣ የዓየር ንብረት ሁኔታና የአብራሪው የችሎታ ማነስ ወይንም በሌሎች ችግሮች ምክንያት የሚመጡ አደጋዎች ይጠቀሳሉ፡፡
ለወደፊት መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ የአውሮፕላን የደህንነት ፕሮቶኮሎች መገምገምና የአውሮፕላን ጥገና ደረጃዎችን ለማሻሻል በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ ጫና እየጨመረ እንደሚገኝ ማወቅ ይቻላል፡፡