Fana: At a Speed of Life!

በትራክተር የሚታረስ መሬት ምጣኔ 5 ሚሊየን ሄክታር ደርሷል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሶስት አመታት በተሰሩ ስራዎች በትራክተር የሚታረስ መሬት ምጣኔ 5 ሚሊየን ሄክታር ደርሷል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ባለፉት ስድስት አመታት በግብርና ላይ የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች የዘርፉን ማነቆዎች መፍታት መቻላቸውንም ተናግረዋል።

ግብርና ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራበት ቢቆይም ከፖሊሲ ጀምሮ የተግባር እርምጃ ከመውሰድ አንጻር በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው አስታውሰው÷ የለውጡ መንግስት ዘርፉን ለማሻሻል ከወሰዳቸው ቀዳሚ እርምጃዎች ዋነኛው የፖሊሲ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ለሜካናይዜሽንና ለመስኖ እርሻ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር በማስገባት በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም በዘርፉ የተከናወነ ትልቅ የፖሊሲ እርምጃ እንደሆነ ጠቅሰው፤ አርሶ አደሮች ትራክተር እና ኮምባይነር ለማግኘት የነበረበትን የፋይናንስ እጥረት ለመፍታት የሚያስችል የባንክ አሰራር በአሁኑ ወቅት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ይህም ለሜካናይዜሽን እርሻ መጎልበት መሰረታዊ ለውጥ መሆኑን ተከትሎ በርካቶችን የማሽነሪ ባለቤት አድርጓል ብለዋል።

የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆኑም ማስቻሉን አስገንዝበዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት አመታት በተሰሩ ስራዎች በትራክተር የሚታረስ መሬት ምጣኔ 5 ሚሊየን ሄክታር ደርሷል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.