የክልልነት ጥያቄው ምላሽ ማግኘቱ ህዝቡ የራሱን ፀጋዎች ማልማት እንዲችል አድርጎታል – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ የክልልነት ጥያቄ መመለሱ ህዝቡ የተፈጥሮ ሀብቱን እንዲጠቀም አስችሎታል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳሩ÷ ብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በመመለሱ ክልሉ በተፈጥሮ የታደለውን የመልማት ጸጋ በአግባቡ እንዲጠቀም እድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ በማዕድን ሀብት የበለጸገ፣ ለግብርና ሥራ የተመቸ ሥነ ምህዳር ያለው እንዲሁም በቡናና ቅመማቅመም ምርት እንደሚታወቅ ጠቅሰዋል፡፡
በግብርና፣ ኢንዱስትሪና፣ አገልግሎት ዘርፍ በክልሉ ከተመዘገቡ 918 ኢንቨስተሮች 52 በመቶ የሚሆኑት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብ በክልልነት ከተደራጀ በኋላ የመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ክልሉ ሲመሰረት ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው የቡና መጠን ከ35 ሺህ ቶን እንደማይበልጥ አስታውሰው፤ አሁን ላይ ወደ 60 ሺህ ቶን ማደጉን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ምርትን ከማሳደግ ባለፈ በሀብት አሰባሰብ ለውጥ ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ ከእርሻ መሬት መጠቀሚያ ግብር በዓመት ይሰበሰብ ከነበረው 18 ሚሊየን ብር ገቢ በ2016 በጀት ዓመት ወደ 220 ሚሊየን ብር ማሳደግ መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡
ይህንኑ ምጣኔ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 400 ሚሊየን ብር ከፍ ለማድረግ መታቀዱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጨማሪም ከህብረተሰቡ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ በተሰበሰብ 1 ቢሊየን ብር የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ተችሏል ብለዋል፡፡