በጎንደር የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎንደር የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር የዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
ከተማ አስተዳደሩ የጥምቀት በዓልን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማክበር ከፀጥታ አካላትና ከማሕበረሰብ የሰላም ዘብ ጠባቂ አባላት ጋር ተወያይቷል፡፡
ተቀዳሚ ም/ከንቲባው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ሁሉም የሰላም ባለቤት በመሆን የጥምቀት በዓልን ያለምንም የፀጥታ ችግር ለማክበር መዘጋጀት አለበት፡፡
ሰላምና ልማት የሚመጣው ሕዝቡ ለጉዳዩ ባለቤት መሆን ሲችል ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከተማዋን ወደ ቀደመ የተሟላ ሰላም መመለስ እንደሚገባ ጠቁመው÷ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከህብረተሰቡ ጋር በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
የፀጥታ አካሉ ከባለፈው ዓመት የወሰደው ልምድና የከተማውን ሰላም ለመጠበቅ በርካታ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ የሰላም ዘብ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
የጥምቀት በዓልን በአስተማማኝ ሁኔታ በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት እንደተጠናቀቀ መገለጹንም የከተማው ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።