በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ የ1 ሚሊየን ዶላር የግዢ ጨረታ ሂደት ተቋረጠ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ የ1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የግዥ ጨረታ ሂደት ማቋረጡን አስታወቀ፡፡
በሕዳሴ ቴሌኮም አክሲዮን ማኅበር ሊከናወን የነበረውን የ1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሶላር ላተርን እና ሆም ሲስተም የግዥ ጨረታ ሂደት እንዲቋረጥ ማድረጉን ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
ለግዥ ሂደቱ መቋረጥ ምክንያት ከሆኑ የጥናት ግኝቶች መካከል÷ የጨረታ ሠነድ ለተጫራቾች በግልፅ እና በፍትሐዊነት አለመቅረቡ፣ የቴክኒክ ኮሚቴ ግልፅ በሆነ መልኩ ግምገማ አለማድረጉ፣ ለዕቃው ጥራት የተሰጠው የቴክኒክ ምዘና ነጥብ ዝቅተኛ መሆን የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ለሌሎች ተያያዥነት ላላቸው የምዘና ነጥቦች ከፍተኛ ነጥብ መሰጠቱ፣ የግዢ መመሪያን በከፍተኛ ደረጃ መጣሱ እና በግዥ ጨረታ ሂደቱ ያልተገባ ትስስርን በመፍጠር ለጥቅም ግጭት ክስተት መጋለጡ የሚሉት በምክንያትነት ተገልጸዋል፡፡