Fana: At a Speed of Life!

ካሉበት ሆነው ኃይል ለመግዛት የሚያስችል ስማርት ቆጣሪ እየተገጠመ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ካሉበት ሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት እንዲችሉ ነባር ቆጣሪዎችን በኤስ ቲ ኤስ ስማርት ሜትር እየቀየረ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

እስከ አሁን በባልደራስ ኮንዶሚኒየም እና በመካኒሳ ባቱ አንድ ኮንዶሚኒየም ከ1 ሺህ 600 በላይ ነባር ቆጣሪዎች በኤስ ቲ ኤስ ስማርት ቆጣሪዎች መቀየር መቻሉንም ነው ተቋሙ የገለጸው፡፡

በቀጣይ ሦስት ወራት 10 ሺህ ነባር ቆጣሪዎችን ለመቀየር ታቅዶ እየተሠራ ነው መባሉን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኤስ ቲ ኤስ ስማርት ቆጣሪዎች ደንበኞች ወደ ማዕከል መምጣት ሳይጠበቅባቸው ካሉበት ሆነው በእጅ ስልካቸው በመጠቀም ብቻ ኃይል መግዛት እንዲሁም የኃይል አጠቃቀማቸውን መከታተል የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች ኃይል ገዝቶ ለመጠቀም የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት ለመቀነስ ብሎም ከቢል ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ያስችላሉ ነው የተባለው፡፡

በዚህ ፕሮጀክት 500 ሺህ ነባር ቆጣሪዎች ይቀየራሉ ያለው አገልግሎቱ÷ የቆጣሪዎቹ ግዢ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን አረጋግጧል፡፡

ለፕሮጀክቱ ትግበራ በዓለም ባንክ የሚሸፈን ከ48 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉንም ጠቁሟል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.