Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ ዕዳ ሳይሆን ምንዳ እናወርሳለን ብሎ የገባውን ቃል በተግባር እያረጋገጠ ነው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ፓርቲ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም ዕዳ ሳይሆን ምንዳ እናወርሳለን ብሎ የገባውን ቃል በተግባር እያረጋገጠ ነው ሲሉ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

አብርሃም በላይ (ዶ/ር)÷ ብልጽግና ፓርቲ ትክክለኛ የፕሮጀክት አመራርና ውሳኔ በመስጠት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት የማከናወን አቅምን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች የመሰረተ ድንጋይ እየተቀመጠ በጅምር የሚቀሩ በርካታ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ አስታውሰው፤ ብልጽግና ፓርቲ እንዲህ አይነት አሰራሮች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ የኮይሻ የሃይል ማመንጫ እና ከ15 ዓመት በላይ ግንባታው ተቋርጦ የነበረው የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታቸው እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል።

ለዚህም ብልፅግና ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት በጀት በመመደብ፣ የፕሮጀክት አመራር ለውጥ በማድረግ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ እንዲከናወን ማድረጉን አብራርተዋል።

ፓርቲው ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም ዕዳ ሳይሆን ምንዳ እናወርሳለን ብሎ የገባውን ቃል በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

ለዓመታት ተጀምረው የነበሩ የመስኖ ግድቦች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት የሶስት መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እንደሚጠናቀቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ በቂ እና የሰለጠነ የሰው ሃብት መኖሩን ጠቅሰው፤ በመስኖ ልማት ጭምር በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለመውጣት የሚያስችል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.