Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት መንግስታት የሳይበር ወንጀሎችን አስመልክቶ ስምምነት አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት የሳይበር ወንጀልን ለመከላከልና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ማጽደቁን አስታወቀ፡፡

ስምምነቱ በተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት መካከል በ20 ዓመታት ውስጥ የተደረገ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የወንጀል መከላከል ስምምነት ነው።

የኢንፎርሜሽን እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን ያለአግባብ መጠቀም ለሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ እውቅና የሚሰጠው ይህ ስምምነት፤ መሰል ወንጀሎች በሀገራት፣ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ህብረተሰብ ደህንነት ላይ የሚያደርሱትን አሉታዊ ተፅእኖ አጉልቶ የሚያሳይ እንደሆነም ታምኖበታል፡፡

የስምምነት ሰነዱ ከሽብርተኝነት፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እና በኦንላይን ከሚደረግ የገንዘብ ዝርፊያና መሰል ወንጀሎች ዓለም እንዲጠበቅ በትኩረት ለመስራት ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

የሳይበር ወንጀሎች በተጠቂዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖ በመገንዘብ በተለይ ተጋላጭ ወገኖች ፍትህ እንዲያገኙ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

በዚህም በባለድርሻ አካላት መካከል የቴክኒክ ድጋፍ፣ የአቅም ግንባታ እና ትብብር እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፥ ሥምምነቱ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳርን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን መጠቆማቸውን የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.