Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በአፈፃፀሙ ላይ ባካሄደው ግምገማ የአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያዋ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጧል።

ጥምር ኃይሉ ታሕሣሥስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያዋ ያለውን የፀጥታ ሁኔታን ገምግሞ በአጠቃላይ እንደ ሀገር በሁሉም ክልል በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ባለው የፀጥታ ስራ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን አንስቷል፡፡

በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በኮማንድ ፖስት እየተመራ በተከናወነ የፀጥታ ስራ ጋር በቀጥታ በተቆራኘ መልኩ በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ በተካሄደው ተከታታይ ኦፕሬሽን አሁን ላይ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የሚከቱ በጦር መሣሪያ በመታገዝ ተደራጅተው የሚፈፀሙ ወንጀሎች አለመኖራቸውን የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይሉ አረጋግጧል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ የፀጥታ ሁኔታን አስተማማኝ ለማድረግ በተካሄደው ኦፕሬሽን በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በኮንትሮባንድ፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በሀሰተኛ ሰነዶች፣ በእገታ እና በስርቆት ወንጀል ህብረተሰቡን ሲያማርሩ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጥምር ኃይሉ አስታውቋል፡፡

 

በተጨማሪም ሀገራችንን የአደገኛ ዕፅ ዝውውር መዳረሻ ለማድረግ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት በአዲስ አበባ ከተማ ቤት ተከራይተው ሲሰሩ የነበሩ ስምንት የውጪ ሀገር ዜጎች እና አስራ አምስት ኢትዮጵያዊያን አምስት ኪሎ ኮኪዬን አደገኛ ዕፅ፣ የሚዋጡ 189 የታሸገ ኮኪዬን፣ የዕፁ ማሸጊያና መጠቅለያ ማሽን፣ ዕፁ መመዘኛ አንስተኛ ሚዛን እና በርካታ ዕፁን ለማሸግ ከሚያገለግሉ ቁሶች ጋር ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ጥምር ኃይሉ ገልጿል።

በቀጣይ በሀገራችን የሚካሄዱ መንግስታዊና ሃይማኖታዊ በዓላት፣ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲካሄዱ በርካታ የሰው ኃይል ስልጠና በማካሄድ እና በሥራ ላይ የዋሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የፀጥታና ደህንነት ጥምር ኃይል አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.