Fana: At a Speed of Life!

ልዩነትን መፍታትና ልማት ላይ ማተኮር የብልጽግና ቀዳሚ አጀንዳ ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ ለመውሰድ ልዩነቶችን መፍታትና ልማት ላይ ማተኮር የብልጽግና ፓርቲ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመደበኛ ስብሰባው ከመከረባቸው አጀንዳዎች መካከል ሰላምና ልማት ዋነኞቹ መሆናቸውንም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ኢትዮጵያን ከግጭት አዙሪት ለማላቀቅ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ- መንግሥትና አወንታዊ ሰላም ግንባታ ላይ ብዙ ርቀት ተጉዟል ብለዋል፡፡

ለውጡ ያልተዋጠላቸው አካላት የፈጠሯቸውን ግጭቶች በድርድርና በውይይት ማርገቡንም አንስተዋል።

ለአወንታዊ የሰላም ግንባታ መሳካትም ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት፣ የሽግግር ፍትህና የተሃድሶ ተግባራትን ለማከናወን ተግባራዊ ቁርጠኝነቱን በማሳየት ላይ ነው ብለዋል።

መንግሥት ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ባደረገው ጥሪ መሰረት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሰላም በመምጣት የሀገር ጸጥታና ልማትን ለማረጋገጥ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የሀገርን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት የሚያስጠብቁ ጠንካራ የፀጥታ ተቋማት መገንባታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ፓርቲው በአንደኛ ጉባዔው ህዝብን ማዕከል ያደረጉ የብዝሃ-ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማቶችን እንደሚተገብር ቃል መግባቱን አውስተው ፥ በዚሁ መሰረት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገባ ስንዴን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት መንግሥት የገባውን ቃል መፈጸሙን ጠቅሰው፥ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በቱሪዝም ዘርፉም በገበታ-ለሀገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ገፅታ የቀየሩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች በጥራትና በፍጥነት መተግበራቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ስራ መጀመራቸው፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካትና የማዕድን ዘርፉ ላይ መሰረታዊ ለውጦች መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

ፓርቲው የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በገባው ቃል መሰረት የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል በማስገባት ሲቪል ሰርቪሱ ላይ ለውጥ እያደረገ እንደሚጀኝም ጠቁመዋል፡፡

ፓርቲው እንደ ሀገር ያልተሻገርናቸውን ችግሮች በመፍታት አካታች የኢኮኖሚ እድገት፣ ዘላቂ ልማትና ሰላም ላይ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያን እምቅ ጸጋ በመጠቀም ወደ ከፍታዋ ለመውሰድ ልዩነቶችን በውይይት መፍታትና በተባበረ ክንድ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ የብልፅግና ፓርቲ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.