የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት የማበረታቻ ሥራዎች እንደሚጠናከሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና እንዲስፋፉ የተለያዩ የማበረታቻ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በኤሌክትሪካ ተሽከርካሪ ማስፋፊያ ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ከባለድረሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ በርኦ ሀሰን በዚህ ወቅት÷ዘላቂና ለአካባቢ ምቹ የሆነ የትራንስፖርት ስርዓት ለመዘርጋት ከተያዙ አሰራሮች ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋት አንዱ ነው፡፡
ለዚህም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እና እንዲስፋፉ የተለያዩ የማበረታቻ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማምረት ላይ ለሚሰማሩ የሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል፡፡
በረቂቅ ስትራቴጂው ላይ አስተያያትና ጥያቄ ከባለድርሻ አካላት የተነሳ ሲሆን÷አስተያየቶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በአጭር ጊዜ ስትራቴጂው ፀድቆ ወደ ተግባር እንደሚገባ መጠቆሙን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡