Fana: At a Speed of Life!

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ከሰው በበለጠ የማሰብ ችሎታን ይጎናጸፋል – ኤለን መስክ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመጪው ዓመት መጨረሻ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ከሰው በሚበልጥ ሁኔታ የማሰብ ችሎታን ይላበሳል ሲል ቢሊየነሩ ኤለን መስክ ተነበየ፡፡

የቴስላ እና የስፔስኤክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤለን መስክ ይህን ትንቢት የተናገረው፥ የኤአይ ኩባንያው ኤክስኤአይ አውሮራ የተሰኘውን የመጀመሪያውን የምስል አመንጪ ሞዴል ይፋ ሲያደርግ ነው፡፡

“በፈረንጆቹ 2025 መገባደጃ ላይ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የአንድን ሰው የማሰብ ችሎታ ይተካል፤ በፈረንጆቹ 2027/28 ደግሞ የሁሉንም ሰው የማሰብ ችሎታ የመተካት እድሉ እየጨመረ መጥቷል” ሲልም ነው መስክ በኤክስ ገጹ ላይ የገለጸው፡፡

ከዚህ ባለፈ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በ2030 ከሰዎች ሁሉ የማሰብ ችሎታ በላይ የመሆን እድሉ መቶ በመቶ ነው ማለቱን የዘገበው አርቲ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ቁጥጥር ካልተደረገበት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ታዋቂ የሆኑ ሰዎች እና የዘርፉ ተመራማሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ ባለፈው ወር በሞንትሪያል ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ተመራማሪ ዮሹዋ ቤንጂዮ (ፕ/ር) የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማሽኖች ብዙም ሳይቆይ የሰው ልጅ የግንዛቤ ችሎታዎች ሊኖሯቸው እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ይህም ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ በሰው ልጅ ላይ ከባድ አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

ተመራማሪው በአሁኑ ጊዜ የሰለጠኑት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማሽኖች የሰው ልጅን ያጠፋሉ የሚለውን ስጋትም አንስተዋል፡፡

ቤንጂዮ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምክንያት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ልዩነት ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋዎች በመጥቀስ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጂኦ-ፖለቲካዊ መረጋጋትን አደጋ ላይ እንደሚጥልም ነው ያስጠነቀቁት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.