በጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰር መድኃኒት እጥረት ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት አላስቻለም ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰር መድኃኒት እጥረት መኖሩን በሆስፒታሉ በህክምና ላይ ያሉ ታካሚዎች ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሆስፒታሉ ውስጥ ያለው የካንሰር መድኃኒት እጥረት ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲጋለጡ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡
መድኃኒቱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና ኢኮኖሚን የሚፈትን በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የካንሰር ህሙማን ማዕከል ኃላፊና የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር መሃመድ ኢብራሂም እንዳሉት፥ ሆስፒታሉ በዓመት ከ4 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ታካሚዎች የካንሰር ህክምና ይሰጣል።
ኬሞቴራፒን ጨምሮ ሌሎች የካንሰር ህክምና መድኃኒቶች በሆስፒታሉ ሲሰጥ እንደነበር ገልጸው፥ የመድሃኒት እጥረት በሆስፒታሉ በማጋጠሙ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡
ይህም የመድሃኒት እጥረት ላለፉት ወራት እንደዘለቀም ነው የተናገሩት፡፡
ዶክተር መሃመድ እንዳሉትም፥ በዚህ ዓመት ሆስፒታሉ ከጤና ጥበቃና ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር የሦሥትዮሽ ስምምነት መፈረሙን አስታውሰዋል፡፡
ሆስፒታሉ መድሃኒት ሲጠይቅም 50 በመቶውን እንደሚከፍል ገልጸው፥ ግማሹን ደግሞ መንግስት እንደሚሸፍንም ነው የገለጹት፡፡
በዚህም ሆስፒታሉ የካንሰር መድኃኒት እጥረቱ እንዳይከሰት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ በበኩላቸው፥ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው 54 ዓይነት የካንሰር መድኃኒቶችን ግዢ በመፈጸም ወደሆስፒታሎች በቀጣዮች ሁለት ሣምንታት ውስጥ ተደራሽ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም 82 በመቶው መድሃኒት በክምችት ውስጥ እንዳለ አንስተው፥ በሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት 94 በመቶ ያህል ክምችት እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡
የመድኃኒት እጥረት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት መሰል መድኃኒቶች በሀገር ውስጥ ማምረት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ሰለሞን ንጉሴ፥ ለዚህ ደግሞ መንግስት ከሀገር ውስጥና ከውጭ መድኃኒት አምራቾች ጋር በመሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ እና መሰረት አወቀ