ትራምፕ የፓናማ ቦይን መልሰን ልንቆጣጠር እንችላለን ሲሉ አስጠነቀቁ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) ተመራጩ የአሜሪካፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የንግድ መርከቦች መተላለፊያ የሆነውን የፓናማ ቦይ መልሰን ልንቆጣጠር እንችላለን ሲሉ አስጠነቀቁ።
ትራምፕ ይህን ያሉት የፓናማ መንግስት በቦዩ በሚያልፉ መርከቦቻችን ላይ የበዛ ክፍያ እያስከፈለን ነው በሚል መሆኑ ተገልጿል።
“በባሕር ኃይላችንና ንግዳችን ላይ ከፍተኛ ኢፍትሃዊነት ተፈጽሞበታል፤ የፓናማ መንግስት የሚያስከፍለን ክፍያ የበዛ ነው” ሲሉም ተናግረዋል ተመራጩ ፕሬዚዳንት።
ይህ በአሜሪካ ላይ እየተደረገ ያለው የለየለት ዘረፋ በአስቸኳይ መቆም አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቱ ጠንከር ባሉ ቃላትም አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ የፓናማ ቦይን በፈረንጆቹ 1914 ገንብታ ለበርካታ አስርት ዓመታት ስታስተዳደር የቆየች ሲሆን÷በ1999 ደግሞ ለፓናማ መንግስት ማስረከቧ ይታወሳል፡፡
በተያያዘም ዶናልድ ትራፕም ቻይና በአካባቢውና በፓናማ ቦይ አካባቢ ተፅዕኖዋ እያደገ መሆኑን ጠቁመው÷ “ ቦዩን ፓናማ ብቻ ነበር ማስተዳደር ያለባት፤ ቻይና ወይም ሌላ አይደለም ብለዋል።
ቦዩ በፍጹም በማይመለከተው አካል እጅ እንዲወድቅ አንፈቅድም” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ትራምፕ “የሥነ ምግባር እና የሕግ መርሆች ካልተከበሩ የፓናማ ቦይ ሙሉ በሙሉ እና ያለጥያቄ እንዲመለስልን እንጠይቃለን” ማለታቸውን አልጃዚራ ዘግቧል።
የፓናማ ፕሬዚዳንት ሁሴ ራውል ሙሊኖ በበኩላቸው÷ የትራምፕን ማስፈራሪያ ተቀባይነት የሌለው ሲሉ አጣጥለውታል።
ፕሬዚዳንቱ “እያንዳንዷ የፓናማ ቦይና አካባቢው ስኩየር ሜትር መሬት የፓናማ ንብረት ነው ብለዋል።
“የአገራችን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም” ሲሉም በተንቀሳቃሽ ምስል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሰው ሰራሹ የፓናማ ቦይ አትላንቲክን እና ፓስፊክ ውቅያኖስን የሚያገናኝ ሲሆን÷ የዓለም በርካታ መርከቦች የሚተላለፉበትና የሀገሪቱ አንድ አምስተኛ ገቢ የሚሸፍን መሆኑ ተጠቁሟል።