በመዲናዋ 22 ሺህ 700 ኪሎ ግራም የተበላሸ በርበሬ ተወገደ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሊሰራጭ የነበረ ለምግብነት የማይውልና በአፍላቶክሲን የተጠቃ በርበሬ በህብረተሰቡ ጥቆማ ተይዞ መወገዱን የከተማዋ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ግምታዊ ዋጋው 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆነው በርበሬ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አካባቢ ከሚገኝ መጋዘን መያዙ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት የናሙና ምርመራ መሰረት በርበሬው እጅግ በጣም ከፍተኛ አፍላቶክሲን የተገኘበት ሲሆን÷ ከደንብ ማስከበር፣ከፖሊስ፣ከንግድ ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት እንዲወገድ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ማህበረሰቡ ማንኛውንም ምርት ሲገዛ ጥራቱና ደህንነቱን የጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገዛና ሕገ-ወጥ አሰራሮችን ሲመለከት በ8864 ነጻ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡