Fana: At a Speed of Life!

ለ160 ሺህ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ባለፉት አምስት ወራት ከ160 ሺህ በላይ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደተለያዩ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ማድረጋቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት÷ ከተለያዩ ውጭ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ዜጎች መብታቸው፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ለማስቻል እየተሰራ ነው።

በዚህም የውጭ ሀገር የሥራ ገበያ በማፈላለግ፣ መዳረሻ ሀገራትን በመለየትና የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈጸም ዜጎች ሕጋዊ የስራ ዕድል እንዲያገኙ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በሀገራቱ ያለውን የሥራ ፍላጎት በመለየት ተወዳዳሪና ብቁ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ዜጎች የስራ መታወቂያ እንዲኖራቸውና በቂ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የግልጸኝነት ስርዓት እንዲዘረጋ ማስቻሉን አንስተዋል።

ከ6 ሀገራትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈፀም የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷በበጀት ዓመቱ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ያደረጉ ዜጎች ቁጥር ከ160 ሺህ ማለፉን ተናግረዋል ።

ዜጎች መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ህጋዊ የውጭ አገር ስራ ስምሪት ስርአትን ተከትለው ሊሄዱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በደላሎች ተታለው በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት ማቅናት ከእንግልት እስከ ሕይወት ማጣት የሚያስከትል በመሆኑ ዜጎች ራሳቸውን ከመሰል አደጋ መጠበቅ እንዳለባቸው አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.