በኦሮሚያ ክልል እየጨመረ የመጣውን የኮቪድ19 ስርጭት መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በአሳሳቢ ደረጃ ከፍ እያለ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ተናገሩ።
የኮሮና ቫይረስ ከአዲስ አበባ ውጭ በክልል ከተሞች በተለይም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ስርጭቱ ከፍ ብሎ ታይቷል።
በኦሮሚያ ክልል በተለይም ባለፉት ቀናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።
የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታም ባለፉት ቀናት በኮቪድ19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ክልሉን ስጋት ውስጥ እንደጣለው ይናገራሉ።
በተለይም የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በክልሉ ተፈጥረው የነበሩ አለመረጋጋቶች ለቫይረሱ ስርጭት መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል ነው ያሉት።
ወጣቱም እራሱን ከኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራውን በመተው ለቫይረሱ የሚያጋልጡ ነገሮችን ሲያደርግ ተስተውሏል ብለዋል።
አሁን ላይም በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ያለውን የኮቪድ19 ስርጭት ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስም ክልሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የግብርናው ዘርፍ እንዳይጎዳ አርሶ አደሩን የመጠበቅ ስራዎች ላይ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ቫይረሱን ከመከላከል ጎን ለጎንም ምርታማነትን ለመጨመርም የሚረዱ መንገዶች ላይም እየተሰራ ስለመሆኑ አውስተዋል።
በክልሉ የሚገኝ የትኛውም የእርሻ ቦታ ፆም እንዳያድር ከማድረግ ጀምሮ ዘርፉን ሊደግፉ እና ምርታማ ሊያደርጉ የሚችሉ እንዲሁም የወጪ ንግዱን የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ የዜግነት አገልግሎት ስራ ላይ ወጣቱ በስፋት እንዲሳተፍ እየተደረገ ነው ያሉት ወይዘሮ ጫልቱ ከዚህ ቀደም በዚህ አገልግሎት በተሰሩ የከተማ ልማት፣ የበጎ ፈቃድ እና መሰል ተግባራት በቢሊየን ብር የሚቆጠሩ ስራዎችን ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።
እንደ እርሳቸው ገለጻ ወጣቱ ስሜታዊ ከመሆን ተላቆ ሀገር ወዳድ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይኖርበታል።
ሀገር መውደድን ማሳየት የሚቻለውም ሰርቶ በመለወጥ መሆኑን ጠቅሰው ወጣቱ እራሱን፣ ጎረቤቱን እና ሀገሩን የመጠበቅ ሀላፊነት እንዳለበት አንስተዋል።
ወጣቱ የሀገሩን ሰላም በማስጠበቅ እና አርሶ አደሩን በስራ በማገዝ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ስራ ላይ እንዲሰማራም ጥሪ አቅርበዋል።
በዙፋን ካሳሁን