የሽብር ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን እና አካባቢው የሽብር ወንጀል በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ ከ1 ዓመት ከ6 ወር እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው፡፡
በግለሰቦቹ ላይ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን እና አካባቢው የሽብር ወንጀል ሲፈፅሙ በፀጥታ ኃይሎች በተካሄደው ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የሽብር ጥቃት በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ የሰው እና የሠነድ ማስረጃ ማቅረቡን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ በግለሰቦቹ ላይ ክስ መስርቶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ታሕሣሥ 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወንጀለኞቹን ያስተምራል ሌሎችንም ያስጠነቅቃል በሚል ከ1 ዓመት ከ6 ወር እስከ 23 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡