Fana: At a Speed of Life!

ክልሉ ከሻይ ምርት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያገኘ እንዳልሆነ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሻይ ምርት ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያገኘ እንዳልሆነ ገለፀ፡፡

በክልሉ የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተርና የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ጥበቃ ዘርፍ ኅላፊ አቶ በላይ ኮጁአብ የክልሉ ስነ-ምህዳር ለሻይ ቅጠል ምርት ምቹ ቢሆንም ከካፋ እና ሸካ ዞኖች በስተቀር በሌሎች አካባቢ እየተመረተ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

በካፋ ዞን ውሽውሽ የሻይ ልማት ድርጅት በ1 ሺህ 296 ሄክታር መሬት ላይ በሸካ ዞን ደግሞ ኢስት አፍሪካ የልማት ድርጅት በ541 ሄክታር መሬት ላይ ሻይ ቅጠል እያለማ መሆኑን ኅላፊው ለፋና ዲጂታል ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዞኖቹ የሚገኙ 520 አርሶ አደሮች በ463 ሄክታር መሬት ላይ በማምረት ለድርጅቶቹ እንደሚያስረክቡ ጠቁመው፤ በአጠቃላይ በክልሉ የሻይ ቅጠል ምርት ሽፋን 2 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የሻይ ተክል የአፈር አሲዳማነትን ተቋቁሞ ምርት መስጠት የሚችል ቢሆንም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባው ገቢ እየተገኘ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ምርቱን የሚያቀነባብር ኢንዱስትሪ እጥረት፣ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ አለመግባትና የዋጋ ተዋዳዳሪነት አለመኖር ዋንኞቹ ናቸው ብለዋል አቶ በላይ፡፡

እንዲሁም አርሶ አደሩ አምርቶ በተገቢው ዋጋ የሚቀበለው ባለመኖሩ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልሆነ እና በዚህም ምክንያት የምርት ሽፋኑ ሊያድግ እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡

ይህን በእንዲህ እንዳለ ግን የዘንድሮው የምርት ዘመን ከባለፈው ጋር ሲነፃፀር እድገት ማሳየቱን ገልፀው፤ በ2016 የምርት ዘመን 6 ሺህ 654 ቶን ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን አንስተዋል።

ከዚህም 1 ሺህ 500 ቶን ለውጭ ገበያ መቅረቡን ገልፀዋል፡፡

በ2017 ምርት ዘመን ደግሞ 7 ሺህ 200 ቶን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱንና እስካሁም 2 ሺህ 800 ቶን ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 251 ለሀገር ውስጥ ገበያ 549 ቶኑ ደግሞ ለውጭ ገበያ መላኩን ጠቁመዋል፡፡

ይህም የተያዘው እቅድ ግቡን እንደሚመታ አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ በላይ ኮጁአብ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ምርት ለማሳደግም ሆነ ክልሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ባለኃብቶችም ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.