Fana: At a Speed of Life!

የእስያ-አፍሪካ ንግድ ም/ቤት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልግ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከእስያ-አፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ም/ቤት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በእስያና አፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር በዚህ ወቅት÷ኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ፈጠራንና ዘላቂ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን የሀገሪቱ የእድገት ስትራቴጂ ምሰሶዎች ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት አብራርተዋል።

ለስታርትአፖች፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለምርምር ከዓለም አቀፍ አካላትና ከግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ጋር በመተባበር ለጠንካራ የፈጠራ ሥነ-ምሕዳር ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አፍሪካውያንን ባስተባበረ መልኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ሥራዎችን ለመስራት የሚደረጉ ትብብሮችን መደገፍ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የም/ቤቱ ሊቀመንበር ጂዲ ሲንግ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ በኢኖቬሽን ዘርፍ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኗን ጠቅሰው÷ይህንን እድል በመጠቀም በጋራ መስራት እንደሚፍልጉ ገልጸዋል፡፡

በተለይ በስታርትአፕ ልማት፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሰው ሃብት ልማት እና የዘርፉ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ሁለቱ አካላት በኢትዮጵያና በመላ አፍሪካ የኢንዱስትሪዎችን እድገት ለማሳደግ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በምርምርና በአቅም ግንባታ ላይ የበለጠ ትብብር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ሥራ ለመጀመር መግባባት ላይ መድርሳቸውም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.