የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በመጠናቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‘የእንኳን ደስ አላችሁ’ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት በመጠናቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‘የእንኳን ደስ አላችሁ’ መልዕክት አስተላለፉ።
ሙሉ መልዕክቱም እንደሚከተለው ቀርቧል፤
ክቡራትና ክቡራን
ዛሬ ሀገራችን በላቀ ጉጉት የምትጠብቀውን ብስራት የምትሰማበት ዕለት ነው። የዓመታት ልፋታችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰበት፣ የህዳሴው ግድባችን የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌት የተጠናቀቀበት ታሪካዊ ዕለት ነው። በጋራ ጥረታችን ግድባችንን እዚህ ደረጃ ስላደረስነው መላው የሀገራችን ሕዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።
በዚህ ዕለት እኛ ኢትዮጵያውያን ዳግም ሀገር ተኮር ስራ ሰርቶ እንዴት ማሳካት እንደሚቻል አውቀናል፤ ሰርቶ አንድ ምዕራፍ ላይ መድረስ የሚያስገኘውን ደስታ በድጋሚ ማጣጣም ጀምረናል። ይበልጥ የሚያስደስተው ማንም ባልተማመነብን ወቅት በራሳችን ዐቅም ላይ ዕምነት ኖሮን ማሳካት በመቻላችን ነው። አንዳንዶች ሕዳሴው ግድብ ላይ ሙጭጭ ማለታችን ምስጢሩ አይገባቸውም። የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ለመጉዳት አልመን የነደፍነው ተንኮል ይመስላቸው ይሆናል፤ እውነታው ግን ያ አይደለም።
ሕዳሴ ግድባችን የዚህ ትውልድ መለያ ማኅተም፣ ሰርቶ የማሳካት ትእምርት ነው። የዘመናት ቁጭታችን መልስ ማግኘት መጀመሩን የምናበስርበት ፋና ነው። አንገታችንን ሊያስደፉ ሲከጅሉ ለነበሩት ሁሉ የጫኑብንን የድህነትና የኋላቀርነት ሸክም ወዲያ ልናሽቀነጥር መቁረጣችንን ጮክ ብለን የምንናገርበት ድምጻችን ነው። እንግዲህ ”ግድባችን” በሁለት እግራችን መቆም እንደማይሳነን፣ ወደ ከፍታው ለማቅናት የመታጠፊያ ነጥባችን መሆኑን ዓለም በትክክል ይረዳል ብዬ እገምታለሁ።
እነሆ እንደተናገርነው ማንንም ሳናስቸግርና ማንንም ሳንጎዳ ባቀድነው ልክ የመጀመሪያውን ዙር ውኃ ሞልተናል። መስከረምን ጨምሮ፣ ክረምቱ ገና ሁለት ወር ተኩል ይቀረዋል። የዝናቡ መጠንም እየጨመረ ነው። እኛም ፈጣሪ ረድቶን ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ የግድቡ ውኃ ሞልቶ መፍሰስ ጀምሯል። ግድባችን እንኳንስ ጉዳት ይቅርና በተቃራኒው ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል የተናገርነውም አሁን በተግባር ይረጋገጣል። ስንገነባውም ሆነ ወደፊት ስናስተዳድረው ግብጽና ሱዳንን የመጥቀም እንጂ የመጉዳት ሀሳብ በእኛ ዘንድ ፈጽሞ የለም። ሁለቱም ሀገሮች የሚያገኙት ውኃ ሳይቀንስ የመጀመሪያውን ሙሌት ማጠናቀቃችን ለዚህ የተግባር ማሳያ ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን
ይሄ እኛ ያየነውን ግድብ ለማየት፣ የሰማነውን የግድቡን ዜና ለመስማት፣ በመዋጮው ላይ ለመሳተፍ ብዙ ትውልዶችና ብዙ መሪዎች ተመኝተው ነበር፤ ዳሩ ግን አልቻሉም። እኛ እዚህ ዘመን ደርሰን ዓባይ ከዘፈንና ከማስፈራሪያነት አልፎ፣ ማንንም ሳይጎዳ ተገድቦ፣ ግድቡም ውኃ ይዞ ለማየት በቃን። ይሄን ያዩ አይኖቻችንና ብስራቱን የሰሙ ጆሮዎቻችን ምንኛ ዕድለኞች ናቸው?
በህዳሴው ግድብ ስም የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ የነበሩ ጥቂቶች የመኖራቸውን ያህል ግድቡ እውን እንዲሆን ብዙዎች ለፍተዋል፤ ሳይሰስቱ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜና ዕውቀታቸውን ሰውተዋል። ከምንም በላይ አይተኬ ሕይወቸውን ለሕዳሴው የገበሩለትም አሉ። በተከፈለው ዋጋ እነሆ የዘመናት ሕልማችን እውን ሆኗል። ዛሬ የምንወቃቀስበት ጊዜ ሳይሆን የምንመሰጋገንበት ዕለት ነው።
ግድቡን ያቀዱ አመራሮች፣ ፕሮጀክቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች፣ ሌት ተቀን በግድቡ ስራ ተሰማርተው የደከሙ ሰራተኞች፣ በየመድረኩ ኢትዮጵያን ወክለው ስለግድቡ ሲደራደሩ የነበሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ይሄን ዕለት እንድናይ አድርገዋል። ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው መዋጮ ያዋጡ ዜጎቻችን እና በዕውቀታቸው ሲያግዙ የነበሩ ባለሞያዎችን ስም እንዘርዝር ብንል ቀናት ይፈጃል። እንዲሁ በአጠቃላይ የቀድሞዎቹን ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ቀጥተኛም ተዘዋዋሪም ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በሙሉ፣ በዲፕሎማሲውም መስክ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉትን ጭምር ከልብ ሳላመሰግን አላልፍም። እኛ እንደ ሀገር የመውቀስና የመኮነን እንጂ የምስጋና ባህል በመጠኑ ይጎድለናል። ትልቁ ወንዛችን ዓባይ ራሱ የዘመናት ወቀሳችን ሰለባ ነበር። በርግጥ ወቀሳው ያለምክንያት አልነበረም፤ እኛን ትቶ ሌሎችን ሲጠቅም ኖሯል። ከእንግዲህ ዓባይም ለእናት ሀገሩ መልካም አስተዋጽኦ ለማበርከት ከጫፍ ደርሷልና አፍ አውጥተን ልናመሰግነው ግድ ይለናል።
ኢትዮጵያውያን ዓባይን በተመለከተ ሲመኙ ከኖሩበት ረዥም ዘመን አንጻር፣ የህዳሴው ግድብ ቢያንስ የዛሬ ሁለት መቶ አመት መገደብ ነበረበት። መሪዎቻችንና ሕዝባችን ፍላጎት ነበራቸው። ሁኔታዎች ግን አልሰመሩላቸውም። እኛ ግን እነርሱ ያሰቡትን አደረግነው፤ የተመኙትን አየነው፤ የናፈቁትን አሳካነው።
ድል ያስፈነድቃል። በድል ላይ እየፈነደቁ ተንጠልጥሎ መቅረት ግን ሁለት ጉዳት አለው። አንድም የተያዘውን ድል ያስነጥቃል፤ አንድም ለሌላ ቀጣይ ድል በር ይዘጋል። ለዚህ ደግሞ ሁነኛ መፍትሄው ያገኙትን ድል አድንቆና አመስግኖ፤ ነገር ግን እርሱን ተሻግሮ ማለፍ ነው። ልክ ደረጃ እንደሚወጣ ሰው። የደረስንበትን የደረጃ እርከን ለቅቀን ወደ ቀጣዩ የደረጃ እርከን ካልወጣን፣ ወደ ኋላ መመለሳችን አይቀሬ ነው። ወደ ከፍታ መጓዝ የሚቻለው ከሚናፍቁት የደረጃ እርከን ለመድረስ በመጓዝ፤ ሲደርሱበት ደግሞ እርሱን ትቶ ወደቀጣዩ በማለፍ ነው።
የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች
ታላቁ የህዳሴው ግድብ በትልቁ እንዳስተማረን አምናለሁ። የማሸነፍ ምስጢሩ ተስፋ አለመቁረጥ መሆኑን፣ ሀገራዊ ስኬት የሚመዘገበው በትብብር መሆኑን፣ ብልጽግና በትውልድ ቅብብሎሽ የሚገነባ ተከታታይ ስራ መሆኑን፣ ዋጋ ሳይከፍሉበት የሚሳካ አንድም ተወዳጅ ነገር አለመኖሩን ግድባችን አሳይቶናል፤ አስተምሮናል። በአስተዳደርና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ሂደትም አሸናፊነት ሊመዘገብ የሚችለው በትብብር፣ በትውልድ ቅብብሎሽና ተስፋ ሳይቆርጡ በመታገል መሆኑ ግልጽ ነው። በተበታተነ አቅምና እርስ በርሱ በሚሳሳብ ገመድ ጉተታ ማፍረስ እንጂ መገንባት እንደማይቻል የሕዳሴ ግድባችን ሕያው ምስክር ነው።
ለሚለያዩን ዕድል ካልሰጠን፣ ለሚያጋጩን በር ካልከፈትን፣ ለሚያጋድሉን ፊት ከነሳን ገና ብዙ ድሎችን በስኬት እንፈጽማለን። አስበን፣ ዐቅደን፣ ሰርተንና አጠናቅቀን ብልጽግናችንን እውን እናደርጋለን። ሁሌም አባቶቻችን የሰሩትን ታሪክ በመናገር ሳይሆን የራሳችንን አሻራ ጥለን በሠራነው ታሪክ መኩራት እንጀምራለን። ለዚህም ቁርጠኝነታችንን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል።
ማሳካት ከሚገቡን መካከል ግድባችን አንዱ ቢሆንም ከፊታችን ገና ብዙ የቤት ስራዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ የግድቡ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ያለቀና የደቀቀ ጉዳይ አይደለም። ገና ብዙ የዲፕሎማሲ ስራዎች ይቀሩናል። ገና ኃይል ማመንጨት አልጀመረም። አሁን ያሳካነው የመጀመሪያውን ዓመት ውኃ ሙሌት ነው። ይሄም በመጪው ዓመት ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንድናመርት ያስችለናል። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ትኩረት ሰጥተን ከሰራን በ2015 ዓ.ም ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ኃይል ማመንጨት ከሚያስችል ደረጃ ላይ ይደርሳል። እስከዚያው ቀሪ ግንባታዎችን በፍጥነት ማከናወን፣ ለግድቡ የሚሆነውን ገንዘብ ሳያቋረጡ ማሰባሰብ፣ ዲፕሎማሲያዊ ትግላችንን በበቂ ሁኔታ መወጣት ይጠበቅብናል። ሌላው ወሳኝ ተግባር በዝናብ እጥረትም ይሁን በደለል ምክንያት ወደፊት ግድባችን በሙሉ ዓቅሙ ጥቅም እንዳይሰጠን የሚያደርጉ እንቅፋቶችን ከወዲሁ ገለል ለማድረግ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው። ለዚህም በአንድ ድንጋይ ሁለት ዒላማ ለመምታት የሚያስችለውንና ቀደም ብለን የጀመርነው የአረንጓዴ አሻራችንን በስኬት ማጠናቀቅ ያስፈልጋል።
ወንዞቻችን እንዲጠቅሙን ከፈለግን የደን ብርድ ልብስ መልበስ አለባቸው። አፈራችንን ተሸክመው አገራችንን አቋርጠው እንዲሄዱ መፍቀድ የለብንም። ”ችግኝ የመትከያው ምርጡ ጊዜ የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር፣ ሁለተኛው ምርጥ ጊዜ ደግሞ አሁን ነው” ይባላል። እውነት ነው። በዝናብ ማጠር ምክንያት ግብርናችን በየዓመቱ የድርቅ ስጋት ሲደቀንበት ኖሯል። አሁን ደግሞ ስጋቱ ከግብርናችን አልፎ ወደኤሌክትሪክ ኃይል ምንጫችን፣ ብሎም ወደ አምራች ዘርፉ መሸጋገሩ አይቀርም። ስለእዚህ የሕዳሴውን ግድባችንን ሙሉ ለሙሉ ከማጠናቀቃችን በፊት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክለን፣ ተንከባክበን፣ አጽድቀን ዛፍ ማድረግ አለብን። የችግኞች ዘመን አልፎ የደኖች ዘመን መምጣት አለበት። የሐምሌ ወር ሳይጠናቀቅ እያንዳንዱ ቤተሰብ አረንጓዴ አሻራውን ማሳረፍ አለበት።
ውድ ኢትዮጵያዊያን
ይሄ ዓመት የሕዳሴ ቤተሰብን የምንመሰርትበት ዓመት ቢሆን መልካም ነው ። የእዚህ ዓመት የህዳሴ ቤተሰብ ሦስት ነገሮችን ማሳካት ይጠበቅበታል። ቀሪ ግንባታዎችን ለማከናወን የሚያስል ገንዘብ ማሰባሰብ ፣ አረንጓዴ አሻራውን ማሳረፍና የህዳሴን ዘመን ለማየት ራሱን ከኮረናቫይረስ መከላከል።
ሁላችሁም እንደምታውቁት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ፣ የሚታመሙና የሚሞቱ ወገኖቻችን ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። ከሦስት ወራት በፊት በቀን የሚያዙ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ነበር። አሁን ቁጥሩ በቀን ወደ 700 እና ከእዚያ በላይ አሻቅቧል። ኮሮናቫይረስ ከባድ አደጋ ይደቅንብናል ሲባል ውሸት አይደለም። ኮሮና አለ። ኮሮና ሰዎችን እየገደለ ነው። ከእውነታው መሸሽ እውነታውን አያስቀረውም። በሁሉም መሰክ ተጋፍጠን ኮሮናን ማሸነፍ እስካልቻልን ድረስ ሸክማችንን ይበልጡኑ እያጠነከረብን ይመጣል፤ ኮሮናን እኛ ቀድመን ካላጠፋነው እርሱ አጥፊ ችግሮችን ይፈለፍልብናል። በአግባቡ ካሰብንበት ከኮሮና እና ወረርሽኙ ከሚያስከትለው ችግር ለመውጣት መፍትሄው እጅግ ከባድ አይደለም።
የጥንቃቄ ህግጋትን በአግባቡ እስከፈጸምን ፣ የተቸገሩ ወገኖቻችንን እስከደገፍነና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እስከቻልን ድረስ የከፋ ፈተና ላይገጥመን ይችላል። በተቃራኒው ችላ ብለን ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት የሚሆኑ ተግባራትን ከፈጸምን ውጤቱን በጥቂት ወራት ወስጥ በዓይናችን እናያለን።
በብዙ ምክንያቶች የዘንድሮ ክረምት ከእዚህ በፊት እንዳለፉት ክረምቶች አይደለም። መደበኛ ሥራዎችን ተዝናንተን የምንፈጽምበት ወቅት አይደለም። ጊዜ የማይሰጠውን ግብራናችንን እንኳ ብንመለከት በተለየ ስትራቴጂ ወሳኝ ተግባራትን ለመፈጸም መንቀሳቀስ ይገባናል። አንድም መሬት ጦም እንዳያድር፣ አንድም አርሶ አደር ግብአት አጥቶ እንዳይቸገር፣ አንድም የግብርና ባለሙያ ቁጭ ብሎ እንዳይውል ማድረግ ይኖርብናል። ወቅታዊ ወረርሽኝ የምግብ እጥረት እንዳያስከትል ቀድመን መስራት ያለበን ። እንኳን ገጠሩ ከተማው ለግብርና ትኩረት መስጠት አለበት። በየግቢያችን የሚገኙ መሬቶች ሁሉ ቢያንስ የጓሮ አትክልት ሊይዙ ይገባቸዋል።
በተመሳሳይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ በቱሪዝም ዘርፍ፣ በማዕድንና ቁፋሮ ዘርፍና በሌሎችም ዘርፎች ጥንቃቄ ሳይጓደል ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። እንዲህ ካደረግን ያለ ጥርጥር ኮሮናቫይረስን ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙ ጥሎት የሚያልፈውን ጠባሳ ከማንም አገር በተሻለ እኛ መሻገር እንችላለን። ከኮሮና ጋር የምንገጥመውን ትግል በተግባር እንጂ በምኞት አንወጣውም። ችግሩ ቀላል እንዲሆንልን በመጨነቅ ሳይሆን እኛ የተሻልን ስለምንሆንባቸው መንገዶች በማሰብ ነው እያንዳንዱን እንቅፋት መሻገር የምንችለው። ለእዚህም ከሕዳሴ ግድባችን የበለጠ ጥሩ ማሳያ አይገኝም። በድጋሚ እንኳን ደስ ያለን እላለሁ! አመሰግናለሁ!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!