አቶ ሙስጠፌ ተቋራጮች ለግንባታ ጥራት ትኩረት እንዲሰጡ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደገሀቡር ከተማ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን የሚሠሩ ተቋራጮች የግንባታ ጥራትን ለማሳደግ በትኩረት እንዲሠሩ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ አሳሰቡ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ በጀረር ዞን ደገሀቡር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን የሥራ ሂደት ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት፣ የስቴዲየም ግንባታ፣ የአስፓልት መንገድ እና የደገሀቡር ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታን መመልከታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ሶዶ ከተማ በመገንባት ላይ ያለውን የደረጃ አንድ የአስፓልት መንገድ የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።
በግንባታ ሂደቱ ከልማት ተነሺዎች ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮች ስለተፈቱ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ተገብቷል ማለታቸውን የወላይታ ዞን አሥተዳደር መረጃ አመላክቷል፡፡
ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን አሳስበው ለዚህም መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡