ተስፋ አልባው መንገድ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማያውቁትን ሀገር ናፍቀው እና ተስፋ አድርገው ባልተገባ መንገድ ወጥተው መንገድ የቀሩት ብዙዎች ናቸው-በህገወጥ የሰዎች ዝውውር፡፡
እንደሄዱ አለመመለስ የሕገ-ወጥ ጉዞው ምላሽም ሆኗል። ዜጎች በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የሀሰት መረጃ ተታለው ያላቸውን ጥሪት ሽጠው እና ተበድረው ህይወታቸውንም ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡ወደ ሳዑዲ አረቢያና ሌሎች ሀገራት በተለየዩ መንገዶች የተሻለ ኑሮና ስራ ፍለጋ ይሄዳሉ፤ ዛሬም ከሞቀው ቤታቸው ተለይተው በዚህ በህገወጥ መንገድ ሲጓዙ ይታያል፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ዋና ስራ አስፈጻሚ ደረጀ ተግይበሉ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ዋና ስራስፈጻሚው በመደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በአብዛኛው ጊዜ ተጎጅዎቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ገልጸው በእነሱ ላይ የሚደርሰውን የስነልቦና ጉዳትና ተጽዕኖ ለመቅረፍ ከጤና ተቋማት፣ ከማህበረሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን እየሰራን ነው ብለዋል።
መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ከሀገር ከወጡ ሰዎች እስካሁን 150 ሺሕ 121 ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውንም ተናግረዋል።
ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 689 ህጻናት ሲሆኑ 11 ደግሞ አካል ጉዳተኛ ሆነው የተመለሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ተመላሾቹ ከሱዳን፣ ሳዑዲ፣ ከቤሩት ከኦማን እና ከሌሎች ሀገራት የመጡ ናቸውም ብለዋል።
መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት የሚሄዱ ሰዎች ከራሳቸውም አልፎ ለቤተሰቦቻቸው ከባድ ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የገለጹት፡፡ በድንበር ላይ ለመያዣነት ተዳርገው ገንዘብ እንዲያመጡ መጠየቅ፣ ለአካል ጉዳት መዳረግ፣ በተላላፊ በሽታዎች መጠቃት እና ለሞት የሚጋለጡበት እድል ሰፊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የሚፈልጉበት ቦታ ሳይደርሱ እየሞቱ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በመደበኛ ፍልሰት የሚሄዱ ዜጎች ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን በአኢኮኖሚ እንደሚደጉሙ እና ካላስፈላጊ እንግልት፣ ጉልበት ብዝበዛና ከሌሎች ሊደርስባቸው ከሚችሉ ጉዳቶች ራሳቸውን ማዳን እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎች መደበኛ በሆነ ፍልሰት እንዲሄዱ ከስራና ክህሎት ሚኒስትና ሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ እደሚገኝ ጠቁመዋል። ፍልሰተኞች በገንዘብ፣ በእውቀትና በክህሎት ለተወለዱበት ሀገር የሀብት ምንጭ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባቸዋልም ብለዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል ከኩዌት፣ ሊቢያ፣ ከኳታር እና ከሌሎች ሀገራት መንግስት ጋር በቤት ውስጥ ሥራ እንዲሁም የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ሃይል ማሰማራት የሚያስችል የመግባበያ ስምምነት ተፈራርሞ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል፡፡
በህጋዊ መንገድ ለሚጓዙ ሰዎች ስልጠናዎችን በማመቻቸት አሰልጥኖ መብታቸውን አስከብሮ እና በሚፈልጉት የስራ መስክ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ካላስፈላጊ የጉልበት ብዝበዛና እንግልት እንዳይዳረጉ እየተሰራ ነው ብለዋል። ስምምነቱ የዜጎችን መብት፣ ደህንነት እና ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ የሥራ ስምሪት እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያሳድግ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
መንግሥት በሰዎች የመነገድ ወንጀልና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና የዚህ ወንጀል ሰለባ የሆኑ ዜጎችን መብት ለማስከበር የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል፡፡
በቅርቡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባወጣው መረጃ በሀገራችን በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የተሰማሩ 49 ኤጀንሲዎች ባለቤቶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉም ይታወሳል።
በመሆኑም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት የሰዎች ዝውውር ወንጀልን የሚፈፅሙ ሰዎች ዋነኛ አላማቸው ገንዘብ ማግኘት መሆኑን አውቀን ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከል የሁላችን የቤት ሥራና የጋራ ሀላፊነት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል።
በየኔወርቅ መኮንን