ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በማዘዋወርና ይዞ መገኘት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በማዘዋወር እና ይዞ መገኘት ወንጀል የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦች ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሰረተ።
በፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር (1) እና አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር (3) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ በግለሰቦቹ ላይ አቅርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ 1ኛ የመኖሪያ አድራሻው በአማራ ክልል ከሚሴ ከተማ ቀበሌ 04 የሆነው ኡስማን ሀሰን፣ 2ኛ በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ የሆነው ያሲን መሀመድ እና 3ኛ በጥበቃ ስራ የሚተዳደረውና የመኖሪያ አድራሻው በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 03 የሆነው መሀመድ አህመድ ናቸው።
ተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾቹ የፀና ፍቃድ ሳይኖራቸው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያን ለማዘዋወር በማሰብ 1ኛ ተከሳሽ በጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡00 ሰዓት ሲሆን ከጋምቤላ ክልል መንገሻ ወረዳ በመነሳት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ በኩል ወደ አማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ከሚሴ ከተማ ለመሄድ በሚያሽከረክረው ኮድ 2-ሲ-05973 አ/አ በሆነ ላንድክሩዘር መኪና እየሄደ እያለ በፖሊስ አባላት ተይዞ በተደረገ ፍተሻ ሶስት ታጣፊ ክላሽ፣ አራት ባለሰደፍ ክላሽ፣ በተጨማሪም አራት የወግ ቁጥር የሌላቸውና የማይታዩ ታጣፊና ባለሰደፍ ክላሾች፣ ዘጠኝ የጥይት ካዝናዎች፣ ስድስት የክላሽ ጥይቶች ይዞ ተገኝቷል።
በሌሎቹ ተከሳሾች ላይ ደግሞ በቀረበው ክስ በጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 12፡00 ሰዓት በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ ልዩ ቦታው መቱ መውጫ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ተከራይተው በሚኖሩበትና 3ኛ ተከሳሽ በጥበቃነት ከሚሰራበት ቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ 22 የክላሽ ማንገቻዎች፣ የግለት መከላከያ መሳሪያዎችን አስቀምጠው የተገኙ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ሰባት የወግ ቁጥር የሌላቸው ክላሾች፣ ስምንት የጥይት ካዝናዎች፣ ሁለት የብሬን አፈሙዝ፣ ሶስት የተነቀለ የሠደፍ ክላሽ እጀታ የሆኑ የጦር መሳሪያዎች በተከሳሾቹ ምሪት ቶፊቅ የተባለ ግብረአበራቸው መኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኘ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ዝርዝር ጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ማዘዋወር እና ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ በዚህ መልኩ የቀረበባቸው የክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸው በኋላ በዋስትና ላይ ክርክር ለማድረግ ፍርድ ቤቱ በይደር ቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ