ህዝባዊ ሰልፉ የህዝቡ ጥያቄና የመንግስት ፍላጎት አንድ እንደሆነ አሳይቷል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ በአማራ ክልለ የተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ የህዝቡ ጥያቄና የመንግስት ፍላጎት አንድ እንደሆነ አሳይቷል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
መንግስት የጀመረውን ሠላምን የማጽናትና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ስራ ህብረተሰቡን በማሳተፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሩ ህዝባዊ ሰልፉን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሕዝባዊ ሰልፉ የተሳተፈው ህዝብ በተለያዩ አካባቢዎች በጽንፈኛው ኃይል የከሸፉ የተቀነባበሩ የቦንብ ፍንዳታዎችና የተኩስ እሩምታ ያልበገሩት ነበር ብለዋል።
ይህ የህዝብ ቁርጠኝነትና የተላለፉት መልዕክቶች ጭብጥ የጽንፈኛው ሃይል፣ ባንዳ አክቲቪስቶችና የደም ነገዴ ሚዲያዎች በአማራ ህዝብ ስም እየነገዱ በዋጋ ሊተመን የማይችል በደልና ስቃይ እያደረሱበት እንደሆነ፤ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ እየወሰደው ያለው እርምጃ ትክክለኛነትና የህዝብ ፍላጎትና ድጋፍ ያለው መሆኑን፤ የፀጥታ ሃይሎች በተለይም መከላከያ ሠራት እየካፈለ ላለው ዋጋ ክብርና አጋርነት፣ ሠላሙን ለማጽናት ያለውን የማያወላዳ አቋም የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
መንግስት ለዚህ ትልቅ አክብሮት እንዳለውና ምስጋና እንደሚያቀርብም ጠቅሰው፥ የህዝቡ ጥያቄና የመንግስት ፍላጎት አንድ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
እነዚህም ሰላምን ማጽናት፣ በየትኛውም አካባቢ ላሉ ነፍጥ ያነገቡ አካላት የሰላም በር ክፍት ማድረግ፣ ልማትን ማስቀጠልና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር፣ ሠላምን የማጽናትና የዜጎችን ድህንነት የማስከበር ስራ ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።