ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋወሪ ደላላዎችን ሰንሰለት ለማቋረጥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ-ወጥ የሰው አዘዋወሪ ደላላዎች የዘረጉትን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ በተለያዩ ሁነቶች መከበሩን በሚኒስቴሩ የብሄራዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው ተናግረዋል፡፡
ቀኑ በተለያዩ መንገዶች ለፍልሰት የተዳረጉ ዜጎች ያበረከቱት አስተዋፅኦ የሚታወስበት መሆኑን ሃላፊው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ስለ ሕገ-ወጥ እና መበደኛ ፍልሰት እንዲሁም በፍልሰተኞች ክብርና ደህንነት ጥበቃ ላይ ግንዛቤ የሚፈጠርበት ቀን መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያ የፍልሰተኞች መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ መሆኗን ጠቁመው÷ አሁን ላይ ከ1 ሚሊየን በላይ ፍልሰተኞችን ከ26 ሀገራት ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የተሻለ ሕይወት ፍለጋ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደተለያዩ ሀገራት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ወጣቶች ደላሎች በዘረጉት ሰንሰለት ተታልለው የሚያደርጉት ሕገ-ወጥ ፍልሰት ለዘርፈ ብዙ ጉዳት እየተዳረጉ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ሕገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል ጥረት እያደረገች ቢሆንም የደላሎች ሰንሰለትና ዘዴ መቀያየር ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡
ስለሆነም በምርምር ታግዞ ድንበር ዘለል የሆኑ ደላሎችን ሰንሰለት በመበጣጠስ ሕገ-ወጥ ፍልሰትን ለመቆጣጠር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ለሕገ-ወጥ ፍልሰት ዋነኛ ምክንያት የሆነው የስራ እድል እጥረት ላይ በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ከምንጩ ለማድረቅም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትብብር እና በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ