Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል በተሟላ ሁኔታ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት መደረጉ ይቀጥላል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተካሄደውን ህዝባዊ ሰልፍ አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ህዝቡ በነቂስ በመውጣት ሰላም እንዲሰፍን፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ በንፁሀን ላይ ግፍ እየፈፀሙ የሚገኙ ፅንፈኛ ኃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ፣ መንግስት በተደጋጋሚ እያቀረበ ለሚገኘው የሰላም ጥሪ ድጋፍ እንደሚቸር በይፋ ድምፁን አሰምቷል፣ እጅግ በጣም እናመሰግናለን ብለዋል።

በቀጣይም ክልሉ በተሟላ ሁኔታ ዳግም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን የሚቀጥል ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።

መንግሰት ለሰላም፣ ለውይይትና ድርድር የምትጠልቅ ጀምበር እንደሌለችም ደጋግሞ ያረጋግጣል ብለዋል።

ስለሆነም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በኃይል አማራጭ የሚገኝ መፍትሔ አለመኖሩን በመረዳት በዛሬው ሰልፍ ጨምሮ ሕዝቡ በተደጋጋሚ እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እየታየ እንደሚገኘው በአስቸኳይ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል በመልዕክታቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.